
ባሕር ዳር: ኅዳር 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 32 ብሔረሰቦች የሚኖሩበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የብሔር ብሔረሰቦች በዓልን ለማስተናገድ ዕድል አግኝቶ የተለያዩ ዝግጅቶች ሲያደርግ መቆየቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናግረዋል፡፡ ርእሰ መሥተዳድሩ በአርባምንጭ በሰጡት መግለጫ በዓሉ ብሔራዊ ተነሳሽነትን የሚፈጥር፤ ዜጎች የራሳቸውን ድርሻ ወስደው ለሀገራዊ ልማት እና ብልጽግና እንዲተጉ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በዓሉ አንድ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብን የመፍጠር ትልምን ዕውን የሚያደርግ እንደኾነም ርእሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ አብራርተዋል። የፌዴራል ሥርዓቱ በፈጠረው ዕውነተኛ ዴሞክራሲ የደቡብ ክልል ተጠቃሚ እንደኾነ በአግባቡ የሚታይ በመኾኑ ኢትዮጵያውያን በአርባምንጭ ሲገኙ ይህንን እንዲረዱ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።
በዓሉ ልዩነት የሚፈጥሩ ችግሮችን በመፍታት የሚያቀራረቡ ሀገራዊ እሴቶችን ለማጎልበት ብሎም አንደኛው ከሌላኛው ጋር እንዲናበብ የሚያስችል ስለመኾኑም ርእሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ አስረድተዋል። ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ ከተማ ኾነው አንድ ስለሚያደርጓቸው የጋራ ጉዳዮች አንዲመክሩ ዕድል የሚሰጥ ነውም ብለዋል።
የብሔረሰቦች በዓል ወቅታዊ እና ሰው ሠራሽ የኾኑ መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታት የመወያየት እና የመመካከር ዕድል የሚፈጥር መኾኑንም አንስተዋል፡፡ እንደ ሀገር ብዝኀ ኢኮኖሚ በመፍጠር ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ በሚሠራው ሥራ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የራሱን ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚያስችለውን በግብርና እና በቱሪዝም ዘርፍ ሰፋፊ ሥራ እየሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በሀገር ደረጃ የከተሞችን ልማት የሚያነቃቃው የኮሪደር ልማት በክልሉ ከተሞችን እያስዋበ ነው ብለዋል፡፡ ርእሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ የኮሪደር ልማቱ የቱሪዝም አቅሙን ከከተሞች ጋር አስተሳስሮ በማሳደግ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ስለመኾኑም አስረድተዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ በዓሉን በተሻለ መንገድ ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ ነውም ብለዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን – ከአርባምንጭ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!