
ባሕር ዳር: ኅዳር 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአንድን ሀገር ዕድገት ከሚያፋጥኑ ቁልፍ ጉዳዮች መካከል መረጃ አንዱ ነው፡ለዕድገት መሠረት የኾነውን መረጃ በማበልጸግ ብሎም ከመረጃ ላይ ተመስርቶ ዕቅድን በማቀድ መተግበር ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ከወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሰባት ክስተቶች መካከል ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻ፣ ፍች እና ጉዲፈቻ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ማስተዋል አለባቸው የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል ለማድረግ ወሳኝ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ የሕዝብ ቁጥር መረጃ መታወቁ በፌዴራል ደረጃም ይኹን በክልል ደረጃ ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ወሳኝ ጉዳይ ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡
በአማራ ክልል ለዞኖች እና ለከተማ አሥተዳደሮች ፍትሐዊ የበጀት ድልድል ሥርዓት እንዲዘረጋ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አሰተዋጽኦው ክፍ ያለ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት፡፡ በወሳኝ ኩነት የሚሠራው ሥራ ለስታትስቲክስ ሥራም አገልግሎት ይሰጣል ነው ያሉት፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዋ በአብዛኛው ፍርድ ቤት ላይ የሚታዩ የተለያዩ የይገባኛል ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ፍርድ ቤቶች ከወሳኝ ኩነት የሚመጣላቸውን የምስክር ወረቀት ተንተርሰው ፍትሕን ለማስፈን በሚሠሩት ሥራ ላይ ጠቀሜታው የጎላ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡
አኹን ላይ ስለ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኅብረተሰቡ ያለው ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ ኅብረተሰቡ ጠቃሚነቱን ተረድቶ በተነሳሽነት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እያካሄደ ይገኛል ነው ያሉት፡፡ ለምዝገባ አመች ይኾን ዘንድም ለእናቶች “የአንድ ማዕከል ምዝገባ” በወለዱበት ተቋም ልጆቻቸውን በማስመዝገብ የምስክር ወረቀት እንዲወስዱ እየተደረገ ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡ ይህም አሠራር የተለያዩ ወጭዎችን በመቀነስ ጊዜንም እንደሚቆጥብ ነው የገለጹት፡፡
የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ማስተዋል አለባቸው ይህ አሠራር አዋጭ ኾኖ በመገኘቱ በ75 ተቋማት ተጀምሮ የነበረው የምዝገባ ሂደት ወደ 122 የጤና ተቋማት በማሳደግ የምዝገባ ሂደቱ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ መረጃዎች ምን ያክል ሕጻናት ተወልደዋል፣ ምን ያህል ሰዎች በምን በሽታ ሕይዎታቸውን አጥተዋል፤ ምን ያህል የጋብቻ ተቋማት ተመስርተዋል፤ ምን ያህል የጋብቻ ተቋማት ፈርሰዋል፤ ምን ያህል ልጆች ለጉዲፈቻ አሳዳጊ ተሰጥተዋል የሚሉት ተመዝግበው እንደ አማራ ክልል መረጃው ተጠናክሮ ለሚመለከተው አካል እንደሚሰጥም አስገንዝበዋል፡፡
ይህ መረጃ ባለመድረሱ እንደሀገር ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል እንዳይኖር ያደርጋል ነው ያሉት፡፡ እንደግለሰብም ቢኾን የሚፈልጉትን ጥቅም በአግባቡ እና በጊዜው እንዳያገኙ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡ ማንኛውም ተግባር የሚከናወነው ከመረጃ በመነሳት ነው ያሉት ኀላፊዋ ማኅበረሰቡ ኩነቶችን በመመዝገብ የክልሉን መረጃዎች ሙሉ ለማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊወጣ እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!