
ባሕር ዳር: ኅዳር 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመማር ማስተማር ሥራውን በተሟላ መንገድ ለማስኬድ የክልሉ ወቅታዊ የሰላም እጦት እንቅፋት እንደኾነበት መምሪያው አስታውቋል። ተማሪ ደጀን አስፋዬ በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዙሪያ ወረዳ ሕዳሴ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ መምህራን ትምህርቱን ለመሸፈን ከመደበኛው ሰዓት ውጭ በመጠቀም እያስተማሯቸው መኾኑን ይናገራል።
ተማሪ ደጀን ከ9ኛ እስከ 11ኛ ክፍል ያሉ የተለያዩ ዓመታት የፈተና ወረቀቶችን በመሥራት እና የ24 ሰዓታት የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እንዲኖር በማድረግ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ መምህራን ጥረት እያደረጉ መኾናቸውን ተናግሯል፡፡ ተማሪ ደጀን የ12ኛ ክፍል ፈተናን የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ለመማር ሰላም መስፈን አለበት የሚል ፅኑ እምነት አለው።
የሀገር ሰላም መኾን ተምረን ውጤታማ ለመኾን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው የምትለው ተማሪ ራቢያ ጌታቸው ትምህርት በመጀመሩ በጣም ደስ ብሏታል። የተሻለ ውጤት አምጥታ ወደ ቀጣይ ክፍል ለመሸጋገር ፕሮግራም በማውጣት ከጓደኞቿ ጋር እንደምታጠናም ነው የገለጸችልን፡፡ የመማር ማስተማሩን ሥራ በውጤታማነት ለማስኬድ ሁሉም አካባቢ ሰላም መኾን አለበት ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዙሪያ ወረዳ ሕዳሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር መሐመድ አብዱ መሐመድ ናቸው፡፡
የሕዳሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ2017 ዓ.ም የተማሪ ቅበላ 2 ሺህ 171 ተማሪ በእቅድ ቢይዝም የተመዘገቡት ግን 696 ተማሪዎች ብቻ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህም የእቅዳቸው 30 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ ከ9ኛ እስከ 11ኛ ክፍል የመማሪያ መጻሕፍት አንድ ለአንድ የታደለ መኾኑን የገለጹት ርእሰ መምህሩ የ12ኛ ክፍል የመማሪያ መጻሕፍት እጥረት መኖሩን ግን ተናግረዋል። ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አስረድተዋል፡፡
በትምህርት ቤቱ አሁንም ድረስ የሚመጡ ተማሪዎችን በመቀበል እና በመመዝገብ የማካካሻ ትምህርት በመስጠት የማብቃት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ርእሰ መምህሩ ገልጸዋል፡፡ በዞኑ በ2017 ዓ.ም ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤት 768 ሺህ ተማሪዎችን ለማስተማር በእቅድ ተይዞ 435 ሺህ ተማሪዎችን በመመዝገብ ወደ ሥራ እንደገቡ የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ዓለምነው አበራው ገልጸዋል፡፡
በዞኑ 1 ሺህ 210 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 68 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን የገለጹት ኀላፊው ከነዚህ ውስጥ 70 የአንደኛ ደረጃ ትምህር ቤቶች እና 4 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት ምዝገባ እንዳልጀመሩ ተናግረዋል፡፡
ኀላፊው አክለውም በዞኑ ትምህርት ሳይቆራረጥ ሙሉ በሙሉ የመማር ማስተማር ሂደቱ የተጀመረባቸው አምስት ወረዳዎች ብቻ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ አሁንም ቢኾን ወደ ትምህር ቤት የሚመጡ ተማሪዎችን ያለማቋረጥ በመመዝገብ ፣ ክትትል በማድረግ እና የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
የመጻሕፍት ስርጭቱን ለማሟላት ክልሉ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር እንደመደበ የተናገሩት ኀላፊው መጻሕፍቱ ታትመው 50 በመቶ የሚኾኑ ወረዳዎች ለተማሪዎቻቸው ማሰራጨታቸውን ገልጸዋል፡፡ መምሪያ ኀላፊው እንዳሉት ህጻናት ምንም ዓይነት የመሣሪያ ድምጽ መስማት አይፈልጉም። ማንኛውም ተማሪ ያለስጋት ወጥቶ በሰላም እንዲመለስ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበትም ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!