በጋራ መምክር እና አቅጣጫ ማስቀመጥ ለጋራ ውጤት እንደሚጠቅም የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡

38

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ላይ እየመከረ ነው። መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች የጋራ ፎረም መሥርተው በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውም ተመላክቷል። የጋራ ፎረሙ ለአራተኛ ጊዜ ዛሬ እየተካሄደ ነው ተብሏል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ መንግሥት ብቻውን ባለው ውስን አቅም ሴቶችን፣ ሕጻናትን እና ለማኅበራዊ ጉዳይ ተጋላጭ የኾኑ ወገኖችን ተጠቃሚ ማድረግ አዳጋች ነው ብለዋል። የክልሉ መንግሥት ባወጣው ፖሊሲ እና ስትራቴጂ መሠረት መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን ነው የተናገሩት።

መንግሥት ያለበትን ክፍተት ለመሙላት እና ሴቶች፣ ሕጻናት እና በማኅበራዊ ጉዳይ ተጋላጭ የኾኑ ወገኖችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከአምስት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ከ170 በላይ ከሚኾኑ ፕሮግራሞች እና ፕሮጀክቶች፣ በክልሉ ከሚገኙ ከ40 በላይ የመንግሥት ተቋማት እና ባንኮች ጋር በጋራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የተሻለ ውጤት ለማምጣት እና ወገኖችን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ የአጋርነት ፎረም መመሥረት እና ማጠናከር አስፈላጊ መኾኑን ነው ያመላከቱት። ሴቶች፣ ሕጻናት እና የማኅበራዊ ጉዳይ ተጋላጭ የኾኑ ወገኖች ያሉባቸውን ተደራራቢ እና ውስብስብ ችግሮች ለማስወገድ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በትብብር መሥራት ወደር የሌለው አማራጭ ነው ብለዋል።

የፎረሙ ዓላማ አጋርነትን በማጠናከር በሴቶች፣ በሕጻናት እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚቀረጹ እና የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ችግር ፈቺ፣ በመረጃ ላይ የተመሠረቱ እና ውጤታማ እንዲኾኑ ማስቻል መኾኑን ነው የተናገሩት። ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን በተለያዩ ዘርፎች ያሏቸውን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር መሥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል። በምክክሩ ያሉ ችግሮችን በመለየት፣ የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ እና በቀጣይ በሚሠሩ ጉዳዮች ላይ የጋራ ሃሳብ መያዝ ዋናው ዓላማ መኾኑን ነው የተናገሩት።

የክልሉ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ተጠቃሚ እንዲኾኑ ችግሮችን እየለዩ፣ መፍትሄዎችን እያስቀመጡ በጋራ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ክልሉ አሁን ካለበት ነባራዊ ሁኔታ ለመውጣት የሚያስፈልገው፣ መደጋገፍ በጋራ መሥራት እና መቀናጀት መኾኑን ገልፀዋል። በጋራ መምክር እና በጋራ አቅጣጫ ማስቀመጥ ለጋራ ውጤት ይጠቅማል ነው ያሉት። በጋራ በመሥራት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል። ክልሉ ካለበት ችግር እንዲወጣ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አስገንዝበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleያልተጌጠበት ወርቅ
Next article435 ሺህ ተማሪዎችን መዝገቦ እያስተማረ መኾኑን የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡