ያልተጌጠበት ወርቅ

75

ባሕር ዳር: ኅዳር 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምድሯ ማዕድናት የመሉባት፣ ሃብት የበዛላት ፣ ያልተነካ ጸጋ የሚገኝባት ናት፡፡ በሁሉም አካባቢዎች አጀብ የሚያሰኙ ጸጋዎች በዝተውላታል፡፡ የተከማቹት ሃብቶች ሀገርን የሚያሳድጉ፣ ሕዝብን በሃብት ማማ ላይ የሚያቆናጥጡ ናቸው፡፡ ነገር ግን ለዘመናት ተቀብረው የተጠቀመባቸው፣ አውጥቶ ያጌጤባቸው፣ ፈልፍሎ የከበረባቸው አልነበሩም፡፡

ከወርቅ ላይ ተኝተው የማያጌጡት፣ ከሕብስት ላይ እየኖሩ የሚራቡት፣ ከሥራ ላይ ተቀምጠው ሥራ አጥ የኾኑት ብዙዎች ናቸው፡፡ የሚታዩት እና የማይታዩት፣ የሚዳሰሱትና የማይዳሰሱት ሃብቶች መገኛ ናት፡፡ በየብስም ቢሉ በባሕር፣ በሜዳ ቢሉ በተራራ ተፈጥሮ ያደላት፣ ታሪክ ያከበራት፣ ጸጋ የበዛላትእና የበዛባት ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡

ኢትዮጵያ የማዕድናት ሃብታም እንደኾነች ይነገርላታል፡፡ በምድሯ አያሌ ማዕድናት እንዳሉ ይነገራል፡፡ ነገር ግን በምድሯ የተከማቹትን ሃብቶቿን አልተጠቀመችባቸውም፤ ለዘመናት ቀብራ አስቀምጣቸው ኖረች እንጂ፡፡ ሃብቶቿን ሳትጠቀም ለዓመታት ከውጭ የማዕድን ምርቶችን ስትገዛ ኖራለች፡፡

ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ የማዕድን ባለሙያዎች ኢትዮጵያ በማዕድን ላይ የተሠራች ሀገር ናት ትባላለች ይላሉ፡፡ ለዚህም ማሳያቸው የማዕድኗን ውበት እና ብዛት ስላዩ ነው፡፡

የማዕድን ሃብት በስፋት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች ደግሞ የአማራ ክልል አንደኛው ነው፡፡ በክልሉ አዲስ ተስፋን የሚሰጥ በርካታ የማዕድን ክምችት እንዳለ የማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ይገልጻል፡፡በክልሉ ያለውን ሃብት ለመጠቀም ደግሞ በስፋት እየተሠራ ነው፡፡

በክልሉ ያለው የማዕድን ክምችት የበርካታ ወገኖችን ሕይወት የቀየረ፣ ለክልሉም ተስፋን የሰጠ ነው፡፡ ከአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በማዕድን ሃብት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል፡፡

ማዕድን የሚያወጡ፣ የሚወጣውን ማዕድን ተቀብለው እሴት የሚጨምሩ፣ ወደ ገበያ የሚያቀርቡት ወይም ወደ ውጭ ገበያ የሚልኩት የሥራ እድል ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ወደፊት በስፋት የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብለው ተስፋ ከሚጣልባቸው ዘርፎች መካከልም ማዕድን አንዱ ነው ተብሏል፡፡

የማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ደግሞ ክልሉ በማዕድን ሃብት የበለጸገ መኾኑን በጥናት እያረጋገጥኩ ነው ብሏል፡፡ በየጊዜው በርካታ የማዕድን ክምችት እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ ማዕድን የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት እና የክልሉን ምጣኔ ሃብት ከፍ በማድረግ የራሱ አስተዋጽዖ አለው፡፡

እሴት ተጨምሮ ወደ ውጭ ሀገር ገበያ ሲቀርብ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ከፍ እንደሚልም ተመላክቷል፡፡ በክልሉ እሴት ሊጨምሩ የሚችሉ መሣሪያዎች እየገቡ መኾናቸውም ተገልጿል፡፡ በማዕድን ማስዋብ እና ማስጌጥ የተሰማሩ ባለሙያዎችም የማዕድን ሥራ ውጤታማ መኾኑን ነው የሚናገሩት፡፡

ነገር ግን በሕጋዊ መንገድ ለገበያ አለመቅረቡ እና በሚፈለገው ልክ እሴት ሳይጨመርበት በመቅረቡ ባለው ሃብት ልክ መጠቀም አልተቻለም፡፡ በሕገ ወጥ መንገድ ሲወጣ ደግሞ ገቢ ያሳጣል፤ የሚፈለገው እድገትም አይመጣም ነው የሚሉት፡፡

የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ የማዕድን ሥራዎች ፈቃድ አሥተዳደር ዳይሬክተር ብርሃኑ ታዬ በክልሉ ውስጥ የተለያዩ ማዕድናት መኖራቸው በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ እስካኹን ድረስ በተደረገው ጥናት ከአርባ ያላነሱ ማዕድናት ተገኝተዋል፡፡ እነዚህን ማዕድናት ለማልማት እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ የማዕድን ክምችቱ እና መጠኑ ይለያይ ይኾናል እንጂ በክልሉ በሁሉም አካባቢ በሚባል ደረጃ የማዕድን ሃብት አለ ብለዋል።

የኮንስትራክሽን፣ የኢንዱስትሪ፣ የኢነርጂ ማዕድን፣ የብረት ነክ ማዕድን እና የከበሩ ማዕድናት መኖራቸውን ነው ያመላከቱት፡፡ ማዕድናቱን የማጥናት፣ የማልማት እና እሴት የመጨር ሥራ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

የማዕድን ሃብት ላይ የእውቀት ክፍተት አለ የሚሉት ዳይሬክተሩ ሥራውን በእውቀት እና በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ ነው ያነሱት፡፡ በተለይም በባሕላዊ መንገድ እየተሠራ ያለውን ሥራ ማዘመን ይገባል ብለዋል፡፡

እየተሠራው ባለው የማስተዋወቅ ሥራ እና የማዕድን ሃብቱ እያስገኘው ባለው ጥቅም ምክንያት ባለሀብቶች ወደ ማዕድን ልማት እየተሠማሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ ለበርካታ ባለሀብቶችም ፈቃድ መሰጠቱንም ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ማዕድናት እና ሌሎች ማዕድናት እንዲለሙ ባለሀብቶች በስፋት መግባት አለባቸው ብለዋል፡፡ የባለሀብቶች ስምሪት ከበፊቱ የተሻለ መኾኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ወደፊት ደግሞ ከዚህ የተሻለ በስፋት እንደሚሠማሩ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

የከበሩ ማዕድናትን ወደ ውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በሚፈለገው ልክ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ በማቅረብ በኩል ክፍተት አለ ነው ያሉት፡፡ የተሻለ የሥራ እድል ፈጥሮ፣ እሴት ተጨምሮበት እና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገባ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

ሕገወጥ የማዕድናት ንግድን መከላከል እና መቆጣጠር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ለማዕድን ሃብቱ ትኩረት ማድረግ እና መደገፍ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ሀገር የሚያሳድገውን የማዕድን ዘርፍ መደገፍ እንደሚጠበቅባቸው ነው የተናገሩት፡፡

ማዕድን ላይ ድጋፍ ማድረግ ከተቻለ ራስን የሚያስችል ምጣኔ ሃብት መገንባት ይቻላል ብለዋል፡፡ የማዕድን ሃብት ሲስፋፋ የሥራ እድል እንደሚሰፋ እና በምጣኔ ሃብት ጠንካራ የኾነች ሀገር መፍጠር እንደሚቻል ነው የተናገሩት፡፡

ለአብነት በቅርቡ የተመረቀው የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ለበርካታ ወገኖች በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ የሥራ እድል መፍጠር መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

ሀገራት በማዕድን ሃብት ማደጋቸውን እና እያደጉ መኾናቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያም በማዕድን ሃብት ማደግ የሚያስችል ሃብት እንዳላት ነው ያመላከቱት፡፡

የአማራ ክልል ደግሞ ከፍተኛ ጸጋ ያለው መኾኑን ነው ያወሱት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የምናልመውን ለውጥ ለማምጣት ሁሉም መሪዎች ሥራን በጋራ እና በጠንካራ ክትትል ማከናወን አለባቸው” ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ
Next articleበጋራ መምክር እና አቅጣጫ ማስቀመጥ ለጋራ ውጤት እንደሚጠቅም የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡