
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከተማ ልማት ዘርፍ ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ነው።
በውይይቱ ላይ ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) እንዲሁም የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች እና የተለያዩ ተቋማት ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ የከተማ ክላስተር ተቋማት ሰው ተኮር ሥራዎችን በመሥራት ለውጥ ለማምጣት ወሳኝነት እንዳላቸው ተናግረዋል። በግምገማው ላይም ተቋማት ሰው ተኮር ሥራዎችን በማከናወን በኩል ያሳኳቸውን ተጨባጭ ለውጦች እንገመግማለን ብለዋል።
በየሴክተሮች የተመደቡ የሥራ ኅላፊዎች በውስጣቸው ያለውን የሰው ኃይል ለክልሉ እና ለሀገር ልማት በትክክል ስለማብቃታቸውም በጥልቅ እንዲዳሰስም አሳስበዋል።
ለሥራ አስፈላጊ ናቸው ተብለው የተመሠረቱ አደረጃጀቶች በትክክል ተግባራዊ ስለመኾናቸው እና ተጨባጭ ለውጥ ስለማምጣታቸው ይገመገማሉ ነው ያሉት። የተሻሻሉ ሕጎች እና ደንቦች ለአጠቃላይ ግንኙነት እና ሥራዎች መሳለጥ የነበራቸው ሚናም ቀርቦ መታየት ያለበት ጉዳይ ስለመኾኑ ርእሰ መስተዳደሩ አስምረውበታል።
የሥራ ግብዓቶችን በትክክል እና በአግባቡ መጠቀም ላይ እና ተቋማቱ ያሉበትን አቋም በግልጽ እናያለንም ብለዋል። ሁሉም የተቋማት መሪዎች ባለሙያዎቻቸውን በማስተባበር ለሕዝብ ጥቅም ምን ያህል እየተረባረቡ እንደኾነ ለይተን ለማወቅ በጥልቀት እንወያይበታለን ነው ያሉት። የከተማ ልማት ዘርፍ በርካታ ተቋማትን በውስጡ ያቀፈ በመኾኑ የነዚህ ተቋማት ትብብር እና ለጋራ ዓላማ የመሥራት ተሳትፎ ምን ይመስል እንደነበርም በውይይቱ እንፈትሻለን ብለዋል።
“የምናልመውን ለውጥ ለማምጣት መሪዎች ሥራን በጠንካራ ድጋፍ እና ክትትል መሥራት አለባቸው” ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ አመራሮች ለባለሙያዎች ይሰጡት የነበረው ድጋፍ እና ክትትል እንደሚገመገም፤ የቀጣይ አቅጣጫም እንደሚቀመጥ አብራርተዋል።
የሥራ ግምገማው የነበሩ ችግሮችን ለማስተካከል እና ጥንካሬዎችን በማስቀጠል ዘላቂ የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ስለመኾኑም ተነግሯል።
በርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) የከተሞች የኮሪደር ልማት በተነሳሽነት እየተከናወነ ስለመኾኑ ገልጸዋል። በከተሞች የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የሸማቾች ማኅበራትን የማቋቋም፣ የመደገፍ እና በአግባቡ እንዲሠሩ የመከታተል ተግባር ሲከናወን መቆየቱንም አስታውሰዋል። ይህም በመድረኩ ቀርቦ ጥንካሬ እና ጉድለቱ እንደሚገመገም አመላክተዋል።
ስልጡን እና ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች በመፍጠር ረገድ በተለይም የኢትዮ ኮደርስ ተሳትፎ በተጨባጭ ያስገኘው ጥቅም ቀርቦ እንደሚገመገምም ተናግረዋል።
በጣና ሐይቅ ላይ ሞተር አልባ ጀልባዎችን በማቅረብ ሰፊ የመዝናኛ ቱሪዝም ለመፍጠር እየተሠራ ስለመኾኑም ዶክተር አሕመዲን ሙሐመድ ተናግረዋል።
ዲጂታል ኢኮኖሚን ከመትከል አኳያ የክልሉ የቴክኖሎጅ ተቋማት እንቅስቃሴ ያለበት አቋም ተፈትሾ ጥንካሬው ይቀጥላል፤ ጉድለቶችም ይስተካከላሉ ነው ያሉት።
በመድረኩ ላይ በከተማ ልማት ዘርፍ ውስጥ ያሉ ተቋማት ሁሉም የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸማቸውን አቅርበው ውይይት ይደረጋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!