ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን በደንብ ከተጠቀምንበት ለአማራ ሕዝብ ስጦታ ነው፡፡

46

ባሕር ዳር: ኅዳር 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለዘመናት ያቆየቻቸው የአብሮነት፣ የአንድነት፣ የነጻነት እና የወዳጀነት እሴቶች አሏት፡፡ እነዚህን መልካም እሴቶች ትውልድ ሲተካካ ጠብቃ አዝልቃቸዋለች፡፡ መንግሥታዊ ሥርዓቶቿም የሕዝብ መልካም እሴቶች ተጠብቀው ይኖሩ ዘንድ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ታላቅ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ከልዩነት ይልቅ አንድነት፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር፣ ከመራራቅ ይልቅ መቀራረብ ሲነገር እና ሲተገበር ኖሯል፡፡ ከዓመታት ወዲህ የተፈጠረው ዋልታ ረገጥ የዘውግ ፖለቲካ ግን ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈላት ነው የሚሉት በርካቶች ናቸው።  የዘውግ ፖለቲካ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ሂደት አድራጊ ፈጣሪ ከኾነበት ጊዜ ጀምሮ የልዩነት ድባብ አይሎ ተደምጧል።

ግማሽ ክፍለ ዘመን ባስቆጠረው የዘውግ ፖለቲካ ንቅናቄ ብዙዎች ያለ ግብራቸው ግብር ተሰጥቷቸው፤ ያለ ስማቸው ስም ተበጅቶላቸው አያሌ ችግሮችን አሳልፈዋል፡፡ በእርግጥ ዘውጌ ፖለቲካ የኢትዮጵያን የመንግሥትነት ሥርዓት ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የግፍ ቀማሽ ኾነዋል።

ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ፍፁም ብሔርተኝነት በተቀነቀነባቸው ዓመታት ኢትዮጵያ የቀደመ የአንድነት ክብሯ አደጋ እየገጠመው፣ የልዩነት ሃሳቦች እየሰፉ ሄደዋል። ይሄ ደግሞ ሀገር እና ሕዝብን ዋጋ አስከፍሏል።  የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎቹ ከኢትዮጵያ እና ከሠንደቅ ዓላማዋ ሥር በነጻነት፣ በፍቅር፣ በአንድነት እና በእኩልነት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር መኖር ነው፡፡

ለብቻ ሰጡኝ፣ ለብቻዬም አድርጉልኝ አይደለም፡፡ እውነቴን አትንጠቁኝ፣ ከወንድሞቼ እና ከእህቶቼ አታሳንሱኝ፣ እኩልነት ይገባኛል ነው፡፡ ታዲያ ጥያቄዎቹን የሚያስመልሱለትም፣ ጥያቄዎችን የሚመልሱለትም ሰዎች አጥቶ ለዓመታት በችግር ውስጥ አሳልፏል፡፡ ከዓመታት በኋላ ግን ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ችግር ይፈታል ተብሎ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ዘዴ ተዘይዷል፡፡

ይሄም ዘዴ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በምክክር የሚፈቱበት፣ መልካም ነገሮቻቸውንም የሚያዳብሩበት እና ለመጭው ዘመን መሠረት የሚጥሉበት ሀገራዊ ምክክር ነው፡፡ ሀገራዊ ምክክር የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን የዓመታት ጥያቄዎችን እልባት ሰጥቶ፣ ኢትዮጵያን እፎይ የሚያስብል፣ ጎባጣዎቿን የሚያቀና፣ ቀዳዳዎቿን የሚሰፋ፣ ሰባራዎቿን የሚጠግን፣ ቁስሎቿን የሚያክም፣ የሚፈስሳትን ደም የሚያደርቅ፣ ተስፋዋን እና ሕልሟን የሚያሳምር ነው፡፡

ታዲያ ይሄን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ደግሞ ግድ ይላል፡፡ ተስፋው ዕውን የሚኾነው አጠቃቀሙ ካማረ እና ከሰመረ ብቻ ነው፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ወርቃማ ዕድሎች ያጋጥማሉ፡፡ የተገኙትን ወርቃማ ዕድሎች የሚጠቀሙ ደግሞ በታሪካቸው ወርቃማ ታሪክ ጽፈው ያልፋሉ፡፡

ወርቃማ ዕድሎችን ያባከኑ ግን በታሪክ የሚያስወቅሳቸውን እና ትውልድም የሚቀጣባቸውን ጠባሳ ትተው ያልፋሉ፡፡ ብልህ ደግሞ እንኳን ከራሱ ስህተት ከጎረቤቱ ይማራል፡፡ ትናንት የመታው እንቅፋት ዛሬ አይመታውም፡፡ አንድ ጊዜ የመታውን እንቅፋት ብርቱ መማሪያ አድርጎ ለዘመናት እንቅፋት እንዳይመታው ኾኖ ይጓዝበታል፡፡

ሀገራዊ ምክክር የተሠሩ ስህተቶች የሚታረሙበት፣ ያለፉ ዕድሎች የሚካካሱበት፣ ለዘመናት መፍትሄ አጥተው የተወዘፉ ችግሮች፣ የቁርሾ መነሻ ሕመሞች የሚፈወሱበት፣ ተስፋዎች ደግሞ የሚሠምሩበት ሂደት ነው፡፡ ስለ ምን ቢሉ የተመካከረ ለመፍትሔ የተዘጋጀ ነውና፡፡ በፖለቲካ ትግል ውስጥ ረዘም ላሉ ዓመታት ልምድ ያካበቱት እና አሁን ላይ  የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢኒስቲትዩት ምክትል ፕሬዚዳንት ኾነው እያገለገሉ የሚገኙት ቹቹ አለባቸው (ዶ.ር)  የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ሥርዓታዊ እና መዋቅራዊ ናቸው፤ የሥርዓት እና የመዋቅር ጥያቄዎች ደግሞ የሚፈቱት በውይይት እና በሥርዓት ነው ይላሉ። 

ለአብነት የሕገ መንግሥት፣ የወሰን እና የማንነት፣ የሃሰተኛ ትርክት እና ሌሎች መሠረታዊ የአማራ ሕዝብ  ጥያቄዎች ሥርዓታዊ ናቸው የሚሉት ዶክተር ቹቹ አለባቸው እነዚህን ችግሮች ማስተካከል የሚቻለው ደግሞ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመመካከር መኾኑን ነው የሚያመላክቱት። የአማራን ሕዝብ የሥርዓት እና የመዋቅር ጥያቄዎች ሊፈታ የሚችለው ደግሞ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መኾኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደንብ ከተጠቀምንበት ለአማራ ሕዝብ ስጦታ ነው፤ በደንብ ካልተጠቀምንበት እና ከተበላሸ ደግሞ ሌላ ችግር ነው ይላሉ። የሀገራዊ ምክክሩን በደንብ መጠቀም ካልተቻለ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተፈጠረው ስህተት፣ ከዚያም ተከትሎ የመጣው ችግር ይደገማል ነው የሚሉት፡፡

አሁን 1980ዎቹ አይደለም የሚሉት ዶክተር ቹቹ በዚያ ዘመን የፖለቲካ ውክልናው፣ ብቃቱ እና ንቃተ ሕሊናው እንደዚህ ዘመን አይደለም፣ አሁን በደንብ የነቃ ሕዝብ ያለበት ዘመን ነው ይላሉ፡፡ በክልሉ የተፈጠረው ችግር የክልሉ ሕዝብ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በተገቢው መንገድ እንዳይካተት እና እንዳይሳተፍ ሊያደርገው አይችልም ወይ? ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ ዶክተር ቹቹ የአማራ ክልል ሕዝብ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን በደንብ ሊጠቀምበት እና ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባው ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ 

ካለፈው መማር አለብን፤ በ1980ዎቹ በንቃት ባለመሳተፋችን ያመለጡን ጉዳዮች አሉ፣ ዛሬ ላይ እንደ ድሮው አይደለም፣ በሚገባ ባለመሳተፉ ምን እንደደረሰበት ሕዝቡ አውቋል፣ አሁንም ይሄን መድገም የለብንም ብለዋል። የአማራ ሕዝብ ሥርዓታዊ እና መዋቅራዊ ችግሮች የሚፈቱት በምክክር ኮሚሽን መኾኑን በደንብ ሊገነዘበው፣ ለምክክር ኮሚሽኑም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የምክክር ኮሚሽኑን ከተጠቀምንበት ስጦታ ነው፣ ብዙዎች ጥያቄዎችን ይፈታል፤ የምክክር ኮሚሽኑ ላይ በንቃት መሳተፍ ይኖርብናል ነው ያሉት። በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የክልሉ ሕዝብ በንቃት መሳተፍ እንዳለበትም አስገንዝበዋል። በ1980ዎቹ የተፈጠረው ስህተት በዚህ ጊዜም እንዳይሠራ መጠንቀቅ ይገባል ነው ያሉት፡፡ 
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን በሚገባ ከተጠቀምን በብዙ ጉዳዮች አማራ ተጠቃሚ ይኾናል፤ ካልተጠቀምን ደግሞ የበፊቱ ስህተት ይደገማል ብለዋል ዶክተር ቹቹ። በ1980ዎቹ በሚገባው ልክ አልተወከልኩም፣ ባለመወከሌም ጥቅሞቼን አጥቻለሁ ሲል የኖረው የአማራ ሕዝብ አሁን ግን ያለውን አቅርቦ የሚገባውን ለመውሰድ ዕድል ገጥሞታል ነው ያሉት፡፡

ዕድሉን መጠቀም አለመጠቀም ደግሞ የዚህ ዘመን አደራ ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በፍጥነት ፈትቶ የዘመናት ጥያቄዎቹ መልስ የሚያገኙበትን ዕድል መጠቀም የሁሉም ድርሻ እና ኀላፊነት ነው፡፡ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን እንደ ዋዛ ማየት ግን ዳግም ዋጋ እንደሚያስከፍል አስገንዝበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፍትሕን ማን ያስከብራት?
Next articleየአማራ ክልል የገጠር ዘርፍ የአማራ ክልል የገጠር ዘርፍ ጉድኝት ተቋማት ለሰላሙ ያላቸውን አበርክቶ የሚዳሰስ እና በቀጣይ ጊዜ ተግባራት ላይም አቅጣጫ የሚያስቀምጥ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡