ፍትሕን ማን ያስከብራት?

46

ባሕር ዳር: ኅዳር 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሕዝብ ከቀደምቱ ሕገ ልቦና እና ከፍትሐ ነገሥት ጀምሮ እስከ አሁኑ ሕገ መንግሥት፣ የፍትሐ ብሔር እና የወንጀለኛ መቅጫ ሕጎች ድረስ በሕግ ለመኖር እና ለመዳኘት ጠንካራ ዕምነት፣ ባሕል እና ፍላጎት ያለው ሕዝብ ነው።

በሕግ አምላክ ተባብሎ እና ”ተቆራኝቶ” ሕግ ያውቃሉ እና ይዳኛሉ ወደሚላቸው አካላት መሄድም የግጭት መፍቻ ታሪኩ ነው። በሕግ ከሄደች በቅሎዬ ያለ ሕግ የሄደች ጭብጦዬ፣ በቆረጡት በትር ቢመቱ፤ በመረጡት ዳኛ ቢረቱ እና የመሳሰሉት ሥነ ቃሎቹም ለሕግ ያለው ክብር ማሳያ ማንነቶቹ ናቸው።

ለሕግ እና ለዳኛ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው የአማራ ሕዝብ የሃይማኖት፣ የባሕል፣ የሥነ ልቦና እና የባሕል ልህቀቱ አሁን ድረስ እርሾው አልጠፋም።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታየ ያለው የሕግ ጥሰት እና አሰቃቂ ወንጀል ተነግሮለት የማያልቀውን የሕዝቡን ሕግ አክባሪነት እየበረዘው ይገኛል። ሕግ የሚረቀቅበት እና የሚከበርበት የአማራ ክልል አሁን ላይ እንደቀደምቱ አይደለም። በጊዜ ሂደትም ሊፈጸሙ ቀርቶ ሊታሰቡ የሚሰቀጥጡ ወንጀሎች ሲከሰቱ ተመልክተናል።

በክልሉ የሕግ አክባሪነት ለምን ተሸረሸረ? ለፍትሕ መጓደል ተጠያቂውስ ማን ነው?  እንዴትስ ይስተካከላል ስንል የሕግ ባለሙያ አነጋግረናል። በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አማካሪ ቢንያም ዮሐንስ ማብራሪያ ሰጥተውናል።

ፍትሕ ምን ማለት ነው?
ጸሐፍት በርካታ እና ሰፋ ያለ ትርጉም ቢሰጡትም ፍትሕ ማለት ሕግ ማክበር ነው ይላሉ አቶ ቢንያም። የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚወጡ ሕጎች ይታረማሉ፤ ይታረቃሉ ተብሎ እንደሚታሰብም ገልጸዋል።

ፍትሕ ጉልበተኛው ደካማውን፣ ሃብታሙ ድሃውን፣ ባለሥልጣኑ ዜጋውን እንዳይበድል ለማድረግ ያስፈልጋል። መንግሥት የሚያስፈልግበት አንዱ ምክንያትም ፍትሕን ለማስፈን ነው። ፍትሕን ማስፈን ሀገራዊ እና መንግሥታዊ ሥርዓትን ማስፈን ነው። ፍትሕ ከሌለ እንደማኅበረሰብም መቀጠል አይቻልም ነው ያሉት።

ፍትሕን ለማስፈንም የአንድ ሰው ወይም የአንድ ተቋም ብቻ ኀላፊነት አይደለም። ከግለለሰብ ጀምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እና ተቋማት ተሳትፎ ድምር ውጤት ነው። ፍትሕ ተጓደለ ሲባል ለኅብረተሰቡ ቶሎ የሚታወሱት የፍትሕ ተቋማት በተለይም ፍርድ ቤቶች ናቸው። ነገር ግን ፍትሕ ለማስፈን ሁሉም ድርሻ አለው ብለዋል።

ፍትሕን ሊያጠፉም ኾነ ሊያሰፍኑ የሚችሉት ሂደቶች ከታለፉ በኋላ ነው ወደ ፍርድ ቤት የሚደርሱት ያሉት አቶ ቢንያም ፍርድ ቤቶች የፍትሕ ሂደቱ መቀመጫ መኾናቸውን ጠቅሰዋል።

በፍርድ ቤት አይኗን ተሸፍና ሚዛን እና ሰይፍ በያዘች ሴት የሚወከለው የፍትሕ ሥራ ዳኞች ሰምተው እንጂ አይተው እንደማይወስኑ ማመላከቻ ነው ብለዋል። እናም የተከራካሪ ወገኖችን ክርክር በኅብረተሰቡ ምስክርነት እና በሚመለከታቸው አካላት ማስረጃ ሰጭነት ነው ወደ ፍርድ የሚደርሰው በማለት የክርክር ሂደቱን እና በፍርድ ሂደት የተሳታፊዎችንም ሚና ያስታውሳሉ።

ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ያሉ ሁሉም ተዋናዮች በዕውነት ካልሠሩ በስተቀር ፍርድ ቤት ብቻ ፍትሕ ሊያሰፍን እንደማይችል ነው የገለጹት። በፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ ከሚጀመረው የወንጀል ምርመራ፣ ማስረጃ ማዘጋጀት፣ ተገቢ የሕግ አንቀጽ ጠቅሶ ክስ እስከ መመስረት ድረስ ካልተከናወነ ፍርድ ቤቶች በሚናፈስ ወሬ ብቻ ፍርድ ሊሰጡ አይችሉም ነው ያሉት።

ይሁን እንጂ ፍርድ ቤት ላይም የሙያ ሥነ ምግባር ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመላክተዋል። ዳኞች በነጻነት መዳኘታቸው ለፍትሕ መስፈን አስፈላጊ ነው ሲባል ተጠያቂነት የለባቸውም ማለት እንዳልኾነም ጠቅሰዋል።

የዳኞች ውሳኔ በይግባኝ የመሻሩ አሠራር እንደተጠበቀ ኾኖ የሥነ ምግባር ግድፈትም ከተገኘባቸው ተጠያቂነት የሚከተላቸው መኾኑን አብራርተዋል። ከዚያም አልፎ በዳኝነት ሥራቸው ሂደት በወንጀል የሚያስጠይቅ ሥራም ከተገኘባቸው ተጠያቂ ይኾናሉ ብለዋል።

ኅብረተሰቡ እንዲኾንለት የሚፈልገው እና የሕጉ ድንጋጌ የመቃረን ኹኔታ በሚታይባቸው የፍትሕ ሂደቶች ላይም ትክክለኛውን እና የሚያዛልቀውን የሕግ አግባብ ለሕዝቡ ማስገንዘብ እንደኾነ ነው ያብራሩት አቶ ቢንያም።

በችኮላ ወጥተው ወደ ተግባር የተገባባቸው አንዳንድ አዋጆችም ለፍትሕ መጓደል ምክንያት እንደኾኑ ጠቅሰዋል። መጀመሪያ ሕጎች ሲወጡ ፍትሐዊ መኾን አለባቸው ያሉት አቶ ቢንያም የአማራ ክልል የመሬት አሥተዳደር አዋጅን ማሻሻል አስፈላጊ የኾነበትን ምክንያት በአብነት አንስተዋል። ስለኾነም በችኮላ ሕግ ከማውጣት መታቀብ ለፍትሕ መስፈን ጠቀሜታ እንዳለው አመላክተዋል።

አንዳንድ ሕጎቻችን በ1960ዎቹ የወጡ እና ኢትዮጵያን ለማሠልጠን በሚል ከውጭ ሀገር የተቀዱ ናቸው ያሉት አቶ ቢንያም ለአኹኑ ጊዜ የሕዝቡ ሥነ ልቦና፣ የአኗኗር ዘይቤ እና ሌሎች ጉዳዮችንም የማይመጥኑ እንደኾኑ ነው ያብራሩት።

ባለው የግንዛቤ አናሳነት ምክንያት መንግሥትን እና የዳኝነት አካሉን አንድ አድርጎ የማየት አመለካከቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ነገር ግን የዳኝነት አካሉ ከመንግሥት አካላት አንዱ እና የዳኝነት ነጻነት ያለው እንዲኾን ሕጉ እንደሚደነግግ አብራርተዋል።

የዳኝነት አካሉ ከአስፈጻሚው ገለልተኛ የኾነ እና የወጡ ሕጎችን መሠረት አድርጎ ውሳኔ የሚሰጥ እንደኾነ የገለጹት። የዳኝነት አካሉ ዋና ሥራው ሕግን መተርጎም እንደኾነ የጠቀሱት አቶ ቢንያም ለሕዝቡ እና ለሀገሪቱ የማይመጥኑ ሕጎች ካሉም እንዲስተካከሉ የሚጠየቀው ሕጉን ለሚያወጣው ፓርላማ እና ለተመራጮች ነው ብለዋል።

ዳኛ ሕግን እና ማስረጃን መሠረት አድርጎ ነው የሚሠራው፤ ሕግ ሲተረጎምም ጣልቃ ገብነት አያስፈልገውም ያሉት አማካሪው በጫና ዳኝነትን ለማስቀየር መሞከር ተገቢ አለመኾኑን ገልጸዋል። ኅብረተሰቡም ሊተባበር ይገባል ብለዋል።

ኅብረተሰቡ ስለ ሕግ እና ፍትሕ ያለውን ግንዛቤ ለማሻሻል የንቃተ ሕግ ትምህርት መስጠት ስለሚያስፈልግም የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ጥምረት በመተባበር መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል። ለዚህም ሥራ መጀመሩን አመላክተዋል።

በአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አካሉ በጥምረት በመሥራት የኅብረተሰቡን የፍትሕ ጥማት ለማርካት ሥራ መጀመሩን አቶ ቢንያም ጠቅሰዋል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ፍትሕ በሚሰፍንበት ስልቶች ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተወያይቶ በመግባባት በ2017 የሥራ ዘመን የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ምቹ የሥራ እና የመገልገያ ቦታን በመፍጠር፣ የሥራ ቁሳቁሶችን በማሟላት፣ ዲጂታላይዜሽንን በመተግበር ቀልጣፋ፣ ግልጽ እና ተጠያቂነት ያለው የዳኝነት ሥርዓት በማስፈን በፍትሕ ሥርዓቱ የሕዝብ አመኔታ ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል። ይህንንም እስከ ወረዳ ለማድረስ እንደታቀደ ገልጸዋል።

በመቶዎች ከሚቆጠር ኪሎ ሜትር ርቀት ባሕር ዳር ድረስ የሚመጣን ባለጉዳይ ተንገላትቶ መመለስ እንደሌለበት መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል። ”መዝገብህ አልተመረመረም ማለት ነውር ይሁን ብለን ከሁሉም ዳኞች ጋር መግባባት ላይ ደርሰናል” ነው ያሉት። ያለ አሳማኝ ምክንያት ባለጉዳይን በቀጠሮ ማመላለስ ነውር ነው ተብሎ አቋም መያዙንም ገልጸዋል።
ዲጂታላይዜሽንን በመተግበር ተከራካሪ ወገኖች በወረዳቸው ኾነው በቪዲዮ ኮንፈረንስ መከራከር እንዲችሉ በማድረግ ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን እንዲቆጥቡ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን አቶ ቢኒያም ገልጸዋል።

በግልጽ ችሎት በመዳኘትም ለሕዝብ የመከታተል ዕድል በመፍጠር የሀሜትንም የሥነ ምግባር መጓደልንም በር ይዘጋል ብለዋል።

ግልጽ ችሎቱ በሚዲያውም የሚዘገብ እና ለኅብረተሰቡ የሚተላለፍ ስለሚኾን የሀሰት ምስክርንም ኾነ የዳኝነት አካሄዱን ለሕዝብ ያስተላልፋል። በመኾኑም ሕዝቡ ችግሩ የት ላይ እንደኾነ መረዳት ይችላል። የምስክር ቃል በትክክል ተመዝግቦ እንዲያገለግል ይኾናል። የእያንዳንዱ ችሎት ውሳኔ ሕግ እና ማስረጃን መሠረት አድርጎ መኾን አለመኾኑንም ማየት እና መመዘን ያስችላል።

ሕዝቡ በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ አመኔታ ከሌለው ፍትሕን በጉልበቱ ለማግኘት ይሞክራል። ስለኾነም ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓትን በመገንባት የሕዝብ አመኔታን ለመፍጠር ታስቦ እየተሠራ መኾኑን ነው አማካሪው የተናገሩት።

ኅብረተሰቡ እና ባለ ድርሻ አካላትም ለፍትሕ መስፈን ድርሻቸውን አውቀው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት ምሕረት ጠይቀው መግባታቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር አስታወቀ።
Next articleሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን በደንብ ከተጠቀምንበት ለአማራ ሕዝብ ስጦታ ነው፡፡