ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት ምሕረት ጠይቀው መግባታቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር አስታወቀ።

123

ገንዳ ውኃ : ኅዳር 04/2017 ዓ/ም (አሚኮ) በዞኑ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አባላት ምሕረት ጠይቀው መግባታቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር አስታውቋል።

የቡድኑ አባል የኾነው እና ለመከላከያ ሠራዊት እጁን የሰጠው ፋሲል ጋሻው እንደተናገረው ማኅበረሰቡን ገንዘብም ይኹን ተሽከርካሪ እያስገደዱ የተለያዩ የዘረፋ ተግባራትን ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ገልጾ መከላከያ ሠራዊት ይረሽናቹሃል የሚል ምክረ ሃሳብ ከመሪዎቻቸው ይነገራቸው እንደነበር አስረድቷል።

ሌላኛው የቡድኑ አባል የኾነው ተመስገን አበበ በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ገልጾ ወጣቱ ፋኖ በሚል ስም ተሸብቦ እና ተጠልፎ ወደ አልኾነ ተግባር ውስጥ ገብቶ በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ችግር ማድረሳቸውን ገልጿል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳደሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አንዳርጌ ጌጡ እንደገለጹት ሕግ ከማስከበር ጎን ለጎን የቡድኑ አባላት መንግሥት ያደረገውን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ወደ ሰላም እንዲመጡ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተደረገ ተከታታይ ውይይት የቡድኑ አባላት የተደረገውን የሰላም ጥሪ በመቀበል በምሕረት መግባታቸውን አስታውቀዋል።

ማኅበረሰቡ ቡድኑን አምርሮ በመጥላቱ እና የሕግ ማስከበሩን ሥራ በመደገፉ በርካታ የጽንፈኛ ቡድን አባላት ወደ ሰላም እየመጡ እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት።

የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የ504ኛ ኮር ምክትል አዛዥ እና የውጊያ አገልግሎት ኀላፊ ኮሎኔል ቾቤ ወርቁ እንደተናገሩት እየተወሰደ ባለው እርምጃ እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ የተሻለ ውጤት የተገኘ መኾኑን ነው ያስረዱት።

ማኅበረሰቡ አሁን የሰራዊቱን ሀገር ጠባቂነት እና የሕዝብ አለኝታነቱን ተረድቶ ጥሩ የኾነ ድጋፍ እና እገዛ በማድረጉ የተሻለ ሰላምና መረጋጋት እየተገኘ ነውም ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰሜን ጎንደር ዞን ከ6 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የመሠረታዊ ዲጅታል ክህሎት ሥልጠና ለመስጠት እየተሠራ ነው፡፡
Next articleፍትሕን ማን ያስከብራት?