
ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብቸና ከተማ ንግድ እና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስማረ ጀምበር “ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት በምሥራቅ ጎጃም ዞን እና በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ ተቋማት ቡድን መሪዎች እና የልማት ድርጅት ሠራተኞች የሰላም ኮንፈረንስ ማካሄዳቸውን ነግረውናል።
የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ማኅበረሰቡን በቅንነት እና በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረው ውስጣዊ አንድነትን በመገንባት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የተግባቡበት ነበር ብለዋል። በዚህ ኮንፈረንስ ተሳታፊ የኾኑት የብቸና ከተማ ንግድ እና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስማረ ጀምበር በኢኮኖሚው ላይ ሳንካ የኾነውን እና የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ያደርገውን የመንገድ መዘጋት ብሎም ነጋዴው ከቦታ ቦታ እንደፈለገ እንዳይንቀሳቀስ መገደቡ ነው ያላሉ።
ይህን ችግር ለመቅረፍም በኮንፈረንሱ የመግባባት እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ መንገዶች ክፍት ከኾኑ ምርት ወቅቱን ጠብቀው ይቀርባሉ፣ ሸማች እና ማኅበራት ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ሥራቸውን በሰፊው እንዲሠሩ ያደርጋል ባይ ናቸው። የቁጥጥር ሥራውንም የተሻለ ያደርገዋል ያሉት የጽሕፈት ቤት ኅላፊው በኮንፈረንሱ ላይ የተነሳውን የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እኩል እሳቤ እንዲኖራቸው ያደረገ መድረክ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት በከተማው በሕገ ወጥ ንግድ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ከ478 በላይ የንግድ ድርጅቶች የንግድ ፈቃድ አውጥተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ሕዝባዊ ውይይቱ ጥሩ መደላድል እንደፈጠረም ነው ያብራሩት፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በጎዳና ላይ የሚነግዱ ሰዎችን በቋሚነት ከጸጥታ አስከባሪዎች እና ከአጋር አካላት ጋር በመነጋገር ሙሉ በሙሉ የማስቆም ሥራ መሠራቱንም ነው የገለጹት።
ኅላፊው ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠል በመድረኩ ላይ የተነሳው የመግባቢያ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሃሳብ ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ያለ ንግድ ፈቃድ የሚሠራው ብቻ ሳይኾን መንገድ መዘጋቱን እንደ ምክንያት በመጠቀም ሕጋዊ ንግድ ፈቃድ ያለው ነጋዴም ደረሰኝ ሳይቆርጥ እና አግባብ በሌለው ዋጋ በመሸጥ የኑሮ ውድነቱ በማኅበረሰቡ ላይ ጫና እንዲያደርስ ማድረጉን ነው ያስረዱት።
በድፍረት ሕግ የማስከበር ሥራን አጠናክሮ ለመሥራት ከሕዝቡ ጋር መግባባት ላይ መድረሳቸውንም ተናግረዋል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ሕገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር እራሱን የቻለ ቡድን እንዳለውም ነው የገለጹት።
ኀላፊው ቡድኑ በር ከበር ጉብኝት በማካሄድ፣ ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ እንዲሁም የኬላ ፍተሻ በማድረግ ሕገ ወጥ ንግዱን በሕጋዊ መረቡ እንዲገባ ሰፊ ርብርብ እያደረጉ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡
የገበያ ንረቱን ለማረጋጋት የተዘዋዋሪ ብድር በጀት በማስመደብ በረጅም ጊዜ ክፍያ የቀበሌ ሸማቾች በከተማ ላሉ የመንግሥት ሠራተኞች ምርትን ማቅረብ እንዲችሉ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!