
አዲስ አበባ: ኅዳር 4/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የመጀመሪያው የካፒታል ገበያ ጉባኤ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች፣ አጋርና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ መንግሥት በፋይናንስ ዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን የሚቀርፉ አዳዲስ አሠራሮችን እየተገበረ መኾኑን ገልጸዋል። የካፒታል ገበያ ምኅዳሩን በማስፋት በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ የግሉን ዘርፍ ጨምሮ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማትን መደገፍ፣ ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠርና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በዘላቂ መሠረት ላይ መገንባት የሚያስችል ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ የካፒታል ገበያው የኢትዮጵያን ማክሮ ኢኮኖሚ የሚደግፍ መኾኑን ጠቅሰው በዘርፉ ብቁ የሰው ኀይል ማፍራትና በጋራ መሥራት ከተቻለ ጠንካራ ኢኮኖሚን መገንባት እንደሚቻል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተልህኩ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ የተረጋጋና ዘላቂ ኢኮኖሚን ለመገንባት የካፒታል ገበያ ወሳኝ ነው ብለዋል። የካፒታል ገበያ ምህዳሩን አካታች፣ ንቁ፣ ችግሮችን መቋቋም የሚችል ኾኖ ከተገነባ የፋይናንስ ሥርዓቱን ቀላል ማድረግና ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ እድሎችና ተግዳሮቶች በሚል ሀሳብም የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!