
ደሴ: ኅዳር 4/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ ”ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት በሃራ ቀጣና በገደራ ቀበሌ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የዘመቻ መምሪያ ኀላፊ ሌተናል ጄኔራል በላይ ስዩምን ጨምሮ የደቡብ ወሎ ዞን እና የተሁለደሬ ወረዳ መሪዎች ተገኝተዋል።
ሕዝቡ እስካሁን የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መኾኑ የመድረኩ ተሳታፊዎች በጥንካሬ አንስተዋል፡፡
ነዋሪዎቹ በቀጣይም ከጸጥታ ኀይሉ ጎን ተሰልፈው የአካባቢያቸውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
ሰላም ከምንም በላይ አስፈላጊ መኾኑን ያነሱት ተሳታፊዎቹ መንግሥት ሰላም የማስከበሩን ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንዲሠራ ነው ጥሪ ያቀረቡት።
የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን እንደ ደቡብ ወሎ ዞን ሰላምን ለማስከበር ዘርፈ ብዙ ውጤታማ ሥራዎች ቢሠሩም ዛሬም ትምህርት ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
ማኅበረሰቡ አሁንም ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሰላሙ ሊሠራ እንደሚገባም ነው የገለጹት።
ዋና አሥተዳዳሪው በውይይት መድረኩ ሕዝቡ ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት ግልጽ የኾነበት ነው ብለዋል፡፡ መንግሥትም ሕዝቡን በማዳመጥ በአካባቢው ሰላምን ለማጽናት እንደሚሠራ አስገንዝበዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የዘመቻ መምሪያ ኀላፊ ሌተናል ጄኔራል በላይ ስዩም መገዳደል ከአማራ ሕዝብ ባሕል እና እሴት ያፈነገጠ ብሎም ፍፁም ተቀባይነት የሌለው አስነዋሪ ተግባር መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ሌተናል ጄኔራል በላይ ስዩም የመንግሥትን የሰላም በር በመጠቀም ወደ ንግግር እና ውይይት በመምጣት ሰላምን ማስከበር እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።
ዘጋቢ፡- ደምስ አረጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!