“የተለወጠ ማኅበረሰብ የማንነቱ ማሳያ የኾኑ የቱሪስት መዳረሻዎቹን ይጠብቃል” የሰሜን ሽዋ ዞን

41

ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ክልል ባለፉት ጊዜያት በተፈጠረው ቀውስ እና ግጭት በርካታ የክልሉ መገለጫዎች ጎልተው እንዳይታዩ ምክንያት ኾኖ ቆይቷል።

ከልሉ አሉኝ ብሎ ከሚኮራባቸው እና ለኢኮኖሚውም የጀርባ አጥንት ኾኖ የሚያገለግለው የቱሪዝብ ሃብቱ ነው።

ቱሪዝም እና ሰላም የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች በመኾናቸው ክልሉ ሰላም ሲርቀው ወደ አማራ ክልል ይገቡ የነበሩ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችም በአንዴ ነበር ያቆሙት።

በዚሁ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ እና ጎሮሯቸውንም ኾነ ቤተሰባቸውን የሚደግፉ ሰዎች እጅግ ተጎድተዋል።

ነገሮችን አርቆ ከማስተዋል እጥረት የመነጨው በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ይዞ የመጣው ጣጣ ብዙ ኪሳራዎችን ነው ያስከተለው።

አማራ ክልል አሉኝ ከሚላቸው ቀደምት ሃይማኖታዊም ኾኑ የማኅበረሰቡ የመገለጫ ቅርሶች የሚገኝበት ሰሜን ሽዋ በተከሰተው ግጭት የነበሩትን የቱሪስት መዳረሻዎች እንደዎትሮው ሁሉ ማስተዋወቅ ከዛም የሚገኘውን ጥቅም ማግኘት ሳይችል ቀርቷል።

ይህን እና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ከማኅበረሰቡ ጋር መወያየት መምከር እና ሰፋፊ መድረኮች መፍጠር ወሳኝ መኾኑን የተረዳው የአማራ ክልል መንግሥት ችግሩን ይፈታል ያለውን ግንዛቤ ለመስጠት ሰፋፊ መድረኮችን እያዘጋጀም እስከ ቀበሌ ድረስ እያወያየ እና ሥልጠናም እየሰጠ ይገኛል።

በዚህ በኩል የሰሜን ሽዋ ዞን የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር የተለወጠ እና የተሻለ አስተሳሰብ ያለው ማኅበረሰብ ለመፍጠር እስከ ቀበሌ ድረስ የወረደ መድረክ አዘጋጅቶ ከማኅበረሰቡ ጋርም እየመከረ ነው።

የሰሜን ሽዋ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ተዋበች ጌታቸው የተለወጠ እና የነቃ የማንነቱ ማሳያ የኾኑ የቱሪስት መዳረሻዎችን የሚጠብቅ ብሎም ከሚገኘው ፍሬ የሚጠቀም ማኅበረሰብ የመፍጠሩ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው የተናገሩት።

ሁሉም ሰው ባወቀው እና በተገነዘበው ልክ የቱሪስት መዳረሻዎችን ይጠብቃል ለዚህም ምቹ ነገር ይፈጥራል የሚሉት መምሪያ ኀላፊዋ ይህን ለማድረግም ከኅብረተሰቡ ጋር ምክክር እየተደረገ ነው ብለዋል።

መድረኮች ማኅበረሰቡ ያሉትን ጸጋዎች ተገንዝቦ ለጸጋዎቹ እና ለሚሰጡት ፍሬ እንዲጨነቅ እና ሰላምን እንዲያረጋግጥ እየተፈጠሩ ያሉ መድረኮች ወሳኝ መኾናቸውን ነው ያስገነዘቡት።

ወትሮውንም ቢኾን ለቱሪዝም ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ ነበር ያሉት የሰሜን ሽዋ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ተዋበች ጌታቸው የተፈጠረው ችግር ተዳምሮ ዘርፉን እጅግ እንደጎዳው ተናግረዋል።

ይህን ዘርፍ ካለበት ችግር አላቆ የተሻለ ሀገርንም ወገንንም የሚጠቅም ለማድረግ እየተፈጠሩ ያሉ መድረኮች ወሳኝ መኾናቸውን ነግረውናል።

ሰው ባለው መረጃ እና ባለው ዕውቀት ልክ ነገሮችን እንደሚከውን የሚናገሩት መምሪያ ኀላፊዋ ማኅበረሰቡ ያለውን ትልቅ የቱሪዝም አቅም በመገንዘብ ይጠብቀው ብሎም ይጠቀምበት ዘንድ በተገኙት መድረኮች ሁሉ እየተሠራ ስለመኾኑም ነው ያብራሩት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበየደረጃው የተፈጠረው የውይይት መድረክ ለግብር አሠባሠቡ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የደቡብ ጎንደር ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ፡፡
Next articleመንግሥት ሕዝቡን በማዳመጥ ሰላምን ለማጽናት እንደሚሠራ የደቡብ ወሎ ዞን አስታወቀ፡፡