
ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት በተቋራጭነት ይዞ የሚገነባውን የባሕር ዳር የኮሪደር ልማት ሥራ በጥራት እና በፍጥነት ለመገንባት በትጋት እየሠራ መኾኑን የድርጅቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ገበያው መንግሥቴ ገለጹ። ለዚህም ከቀኑ ሥራ በተጨማሪም በሌሊት በመሥራት ላይ ነን ብለዋል።
ይሄው የድርጅቱ የምሽት የግንባታ ሥራ በክልሉ እና በከተማዋ ከፍተኛ መሪዎች ተጎብኝቷል። በጉብኝቱ ስለ ግንባታ ሥራው አስተያየታቸውን የሰጡት የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ገበያው መንግሥቴ ድርጅታቸው የሚገነባው የኮሪደር ልማት ርዝመቱ 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር እና ስፋቱም 8 ሜትር መኾኑን ገልጸዋል።
የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ግንባታውን በሁለት ወራት ለማጠናቀቅ እየተጋ መኾኑን የገለጹት አቶ ገበያው ለዚህም የምሽት ሥራዎችን ተቋማዊ ባሕል በማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል። እንደ ተከዜ ድልድይ ያሉትን ፕሮጀክቶች በጥራት እና በፍጥነት በማጠናቀቅ ትላልቅ እና አስቸጋሪ ግንባታዎችን የመሥራት ልምድ አለን። የኮሪደር ልማቱንም በተመሳሳይ ፍጥነት እና ጥራት ሠርተን እናስረክባለን ብለዋል። በቀን ውስጥ በሦስት ፈረቃ በመሥራት ላይ መኾናቸውን ነው ምክትል ሥራ አሥኪያጁ የገለጹት።
ግንባታውን ከጀመሩ ጊዜ ጀምሮ የገጠማቸው ችግር አለመኖሩን የጠቀሱት ምክትል ሥራ አስኪያጁ ኅብረተሰቡም ገንቢ አስተያየት በመስጠት እየተባበረ መኾኑን ገልጸዋል። ባሕር ዳር ስማርት ሲቲ እንድትኾን አሻራችንን ለማሳረፍ ነው የምንሠራ ብለዋል።
የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ኀላፊው ተስፋዓለም አድባሩ ፕሮጀክቱ የእግረኛ፣ የብስክሌት መንገድ፣ የመብራቶች እና የመዝናኛ ቦታዎችም አሉት ብለዋል። በፍጥነት ለማድረስም የቀን እና የሌሊት የሥራ ቡድን ተዘጋጅቶ በፈረቃ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱን ሥራ በቀን እና በሌሊት ከፋፍሎ መሥራት ለፍጥነት፣ የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስ እና የሥራ ባሕልን ለማሳደግም ጠቀሜታ እንዳለው አቶ ተስፋዓለም አስረድተዋል።
ለተደራጁም ኾነ በተናጠል ለወጣቶች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል ብለዋል። የጉልበት ሠራተኞች ተቆጣጣሪ ዮናስ ገድፍ የግንባታ ሥራ ቀዝቅዞ ነበር አኹን ግን መነሳሳት እና ለዜጎችም የሥራ እድል መፈጠር ጀምሯል ብሏል።
“ሌሊት ሲሠሩ የማውቃቸው ቻይናዎችን ነበር ዛሬ ግን በኛም ሀገር ተጀምሯል። ሌሊት መሥራት ከፀሃይ ነጻ ስለኾነ የተሻለ ጉልበት ይኖረናል ብሏል። ባሕር ዳርን በማስዋብ ሥራ በመሳተፌ ደሥ ይለኛል” ብሏል።
የኮሪደር ልማቱ ለአናጺዎች፣ ለግንበኞች እና ለጉልበት ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ለብዙ ቤተሰቦችም እንጀራ ኾኗቸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!