
ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፈው አንድ ዓመት በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የልማት ሥራዎች ላይ ተጽዕኖ ፈጥሮ ቆይቷል፡፡
ከችግሮቹም ውስጥ አንዱ ገቢን ሠብሥቦ ለልማት እና ለመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ለማዋል የነበረው ፈታኝ ሁኔታ ይጠቀሳል፡፡
በደቡብ ጎንደር ዞን በ2017 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዷል፡፡ እስካሁንም የዕቅዱን አንድ አራተኛ መሠብሠብ የነበረበት ቢኾም የፀጥታ ችግሩ ዕቅዱን ለማሳካት እንቅፋት ፈጥሯል፡፡
የተሠበሠበው ገቢም ከ200 ሚሊዮን ብር አለመብለጡን የመምሪያው ኀላፊ ዓባይነው ኀይሉ ገልጸዋል፡፡
የዞን ሠራተኞች በደኅንነት ስጋት ምክንያት ተንቀሳቅሰው ማስተማር እና ገቢንም መሠብሠብ አለመቻላቸው፣ አብዛኞቹ ወረዳዎችም በችግር ውስጥ ኾነው መቆየታቸው የግብር ሠብሣቢ ባለሙያዎችም በሚደርስባቸው ዛቻ በአግባቡ መሥራት አለመቻላቸው በገቢ አሠባሠብ ሥራው ላይ ተጽዕኖ ያደረሱ ምክንያቶች መኾናቸውን ነው አቶ ዓባይነው ያብራሩት፡፡
የፀጥታ ችግሩ ለግብር ከፋዩ ማኅበረሰብም ኾነ ለግብር ሠብሣቢው መሥሪያ ቤት እንቅፋት ኾኖ መቆየቱን የገለጹት አቶ ዓባይነው አሁን እየተደረገ ያለው የሰላም ውይይት ለግብር አሠባሠቡ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አብራርተዋል፡፡
በየደረጃው በሚደረገው የሰላም ውይይትም ግብርን ሠብሥቦ ለልማት የማዋል ጉዳይ ትኩረት መሰጠቱን ነው የገለጹት፡፡
በሰላም ጉዳች ላይ ሕዝብን ከማወያየት በተጓዳኝ እንደ ገቢ አሠባሠብ ያሉ የልማት ሥራዎችም እንዲሠሩ አቅጣጫ የተሰጠባቸው መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡
ስለኾነም በቀጣይም ባለድርሻ አካላትን ጭምር በማስተባበር ገቢን በአግባቡ ለመሠብሠብ ዝግጅት መደረጉን አቶ ዓባይነው ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!