
ባሕር ዳር: ኅዳር 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት በተቋራጭነት ይዞ የሚገነባውን የባሕር ዳር የኮሪደር ልማት ሥራ በጥራት እና በፍጥነት ለመገንባት በትጋት እየሠራ መኾኑን ገልጿል። ለዚህም ከቀኑ ሥራ በተጨማሪም በሌሊት በመሥራት ላይ መኾኑን ገልጿል።
ይሄው የድርጅቱ የምሽት የግንባታ ሥራ በአማራ ክልል እና በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ተጎብኝቷል።
በጉብኝቱ ስለ ግንባታ ሥራው አስተያየታቸውን የሰጡት የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ገበያው መንግሥቴ አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የሚገነባው የኮሪደር ልማት ርዝመቱ 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር እና ስፋቱም 8 ሜትር መኾኑን ገልጸዋል።
ድርጅታቸው ግንባታውን በሁለት ወራት ለማጠናቀቅ እየተጋ መኾኑን የገለጹት አቶ ገበያው ለዚህም የምሽት ሥራዎችን ተቋማዊ ባህል በማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል። እንደ ተከዜ ድልድይ ያሉትን ፕሮጀክቶች በጥራት እና በፍጥነት በማጠናቀቅ ትላልቅ እና አስቸጋሪ ግንባታዎችን የመሥራት ልምድ አለን። የኮሪደር ልማቱንም በተመሳሳይ ፍጥነት እና ጥራት ሠርተን እናስረክባለን ብለዋል።
በቀን ውስጥ በሦስት ፈረቃ በመሥራትም ሥራውን እናቀላጥፋለን። በቀን እና በምሽት የሚሠሩትን በመለየት በኅብረተሰቡ የሚደርሰውን መስተጓጎል፣ መረበሽ እና ብክነቶችን ለመቀነስ ነው የምንሠራው ብለዋል። ግንባታው በጥራት እንዲሠራ እና ለሌሎችም መልካም አርእያ እንዲኾን በአዲስ አበባ ሥልጠና ወስደናል። ለባሕር ዳር የሚመጥን ንድፍ ላይ ቅድመ ልምምድ በማድረግ ዝግጅት አድርገናልም ነው ያሉት አቶ ገበያው። በድርጅታችን ለጥራት ትኩረት መስጠት ባህላችን ስለኾነ በጥንቃቄ ነው የምንሠራ ሲሉም አክለዋል። ባሕር ዳር ስማርት ሲቲ እንድትኾን አሻራችን ለማሳረፍ ነው የምንሠራ ነው ያሉት።
ግንባታውን ከጀመሩ ጊዜ ጀምሮ የገጠማቸው ችግር አለመኖሩን የጠቀሱት ምክትል ሥራ አስኪያጁ ኅብረተሰቡም ገንቢ አስተያየት በመስጠት እየተባበረ መኾኑን ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቱ ኀላፊ ተስፋለም አድባሩ ፕሮጀክቱ የእግረኛ፣ የብስክሌት መንገድ፣ የመብራቶች እና የመዝናኛ ቦታዎችም አሉት ብለዋል። በፍጥነት ለማድረስም የሌሊት የሥራ ቡድን ተዘጋጅቶ በፈረቃ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የግንባታውን ጥራት ለማስጠበቅም ውል እና ሀገር አቀፍ ደረጃዎችን በመጠቀም ቁጥጥር እና ፍተሻዎችን እያስተናገድን እንሠራለን ብለዋል።
ለተደራጁም ኾነ በተናጠል ለወጣቶች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል ብለዋል። የፕሮጀክቶችን ሥራ በቀን እና በሌሊት ከፋፍሎ መሥራት ለፍጥነት፣ የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስ እና የሥራ ባህልን ለማሳደግም ጠቀሜታ እንዳለው አቶ ተስፋለም ገልጸዋል። የጉልበት ሠራተኞች ተቆጣጣሪ ዮናስ ገድፍ የግንባታ ሥራ ቀዝቅዞ ነበር አሁን ግን መነሳሳት እና ለዜጎችም የሥራ እድል መፈጠር ጀምሯል ብሏል።
ሌሊት ሲሠሩ የማውቃቸው ቻይናዎችን ነበር ዛሬ ግን በኛም ሀገር ተጀምሯል። ሌሊት መሥራት ከጸሐይ ነጻ ስለኾነ የተሻለ ጉልበት ይኖረዋል ብሏል። ባሕር ዳርን በማስዋብ ሥራ በመሳተፌ ደሥ ይለኛል በቀጣይሞ ተመሳሳይ ልማቶች በወረዳ እና ዞኖችም እንዲኖር ጠይቋል። በኮሪደር ልማት ግንባታው አስተባባሪ የሺዋሥ አደም በበኩሉ የኮሪደር ልማቱ ለአናጺዎች፣ ለግንበኞች እና ለጉልበት ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ለብዙ ቤተሰቦችም እንጀራ ተከፍቷል ነው ያሉት።
ከምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ገብቼ ከሌሊቱ ስድስት ሠዓት እወጣለሁ፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ ያለው አስተባባሪው በሌሊት መሥራታችን ሥራው እንዲፋጠን ያግዘናል የሥራ ባህልንም ያስተምረናል ብሏል።
ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችም ኖረው ችግረኞች ሠርተው እንዲጠቀሙ ሰላም እንዲኾን ምኞቱን ገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!