
ባሕር ዳር: ኅዳር 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሚያስገነባው የኮሪደር ልማት የምሽት የግንባታ ሥራ በክልሉ እና በባሕር ዳር ከተማ አሦተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ተጎብኝቷል። የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት በተቋራጭነት ይዞ የሚገነባው ይሄው የኮሪደር ልማት ሥራ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ ነው። ከቀኑ በተጨማሪም በምሽት እየተሠራ ሲኾን በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በእውቀት ሽግግርም ጠቀሜታው ጉልህ እንደኾነ እየተገለጸ ነው።
በጉብኝቱ የተሳተፉት የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በሰጡት አስተያየት ልማቱ ለኅብረተሰቡ ይፋ ከኾነበት ጊዜ ጀምሮ የቅድመ ዝግጅት ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል። 22 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማትን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነውም ብለዋል። በግንባታው ሂደት መንገዶች ስለሚቆፈሩ እና ስለሚዘጋጉ ለኅብረተሰቡ ምቹ አይኾኑም፤ እናም ሌሊቱን ጨምሮ በቀን 18 ሰዓት በመሥራት ፈጥኖ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
የመጀመሪያውን ፕሮጀክት በስልሳ ቀናት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው። ቀጣዩን ለማስከተልም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመሠራታቸው የበለጠ ፈጥኖ ይጠናቀቃል ነው ያሉት። በኮሪደር ልማቱ ዘርፈ ብዙ ዕድሎች መኖራቸውን የጠቀሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል፣ ለግብዓት አቅራቢዎች ገበያ እና ለተቋራጮች ንዑስ ኩንትራት በመፍጠር ሰንሰለታዊ ጠቀሜታ እንዳለው ዘርዝረዋል። የኮሪደር ልማቱን ተከትለው የሚሠሩ የከተማውን ደረጃ የሚያሳድጉ ነባር ሕንጻዎችን የማደስ እና የቀለም ቅብ ሥራዎች፣ የመብራት ተከላዎች፣ ባለ ሃብቶች በባዶ ቦታዎች ላይ ማልማት የሚተሳሰር እና ተጠቃሚነት የሚፈጥር ልማት እንደኾነ ገልጸዋል።
የሕጻናት መዝናኛ ቦታዎች፣ የመንገድ ዳር ማረፊያዎች፣ ሻወር እና መጸዳጃ ቤቶች፣ አረንጓዴ ነፋሻማ ቦታዎችን ማዘጋጀትም የኮሪደር ልማቱ አካል መኾናቸዎን ጠቅሰዋል። ይህም ባሕር ዳር ከተማ ምቹ እና ሳቢ እንድትኾን ያደርጋታል። ደረጃዋን የጠበቀች ዓለም አቀፍ ከተማ ኾናም ቱሪስቶች እና ኢንቨስተሮች መርጠዋት እንዲመጡባት እና እንዲቆዩባት ኅብረተሰቡም እንዲጠቀም ለማድረግ ዘላቂ ሥራ ታስቦ እየተሠራ ነው ብለዋል አቶ ጎሹ።
እያንዳንዱ ግንባታ እና ሥራ ሰው ተኮር በመኾኑ ከህጻናት እስከ አረጋውያን ድረስ የሰውን ተጠቃሚነት እና ምቾት ታሳቢ ያደረገ እንደኾነም ገልጸዋል።
አሁን ላይ አመራሩም ኅብረተሰቡም ለሰላሙ ትኩረት በመስጠቱ የሚያጋጥም ችግር የለም። ስለኾነም ልማቱ እየተፋጠነ ነው፤ የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማትም እስከ ኅዳር መጨረሻ 2017 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!