
ባሕር ዳር: ኅዳር 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማትን ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አህመዲን ሙሀመድ (ዶ.ር)፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እና ሌሎችም የክልሉ እና የከተማዋ አመራሮች ጎብኝተውታል።
በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አህመዲን ሙሀመድ (ዶ.ር) በጉብኝቱ በሰጡት አስተያየት ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የአካባቢ ነዋሪዎችን እና ሰውን ተኮር የኮሪደር ልማትን መሥራት አስፈላጊነት ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱ በሁሉም ሪጅኦፖሊታን ከተሞች መጀመሩን እና በባሕር ዳር ደግሞ የምሽቱን ጨምሮ በቀን 18 ሰዓት እየተሠራ ነው፤ በቀጣይም ወደ 24 ሰዓት ያድጋል፤ ሌሎች ከተሞችም በቀጣይ ይሠሩበታል ብለዋል።
በክልሉ 47 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር መንገድ እና 7 ነጥብ 6 ሔክታር አረንጓዴ ልማት የኮሪደር ሥራ ለመሥራት መታቀዱን ገልጸዋል። እስካሁንም ባሕር ዳር 3 ኪሎ ሜትር፣ ጎንደር 360 ሜትር እና ኮምቦልቻም እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ሥራውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ በፍጥነት እየተሠራ ነው። የኅብረተሰቡን ጥያቄ ለመፍታት እና የከተሞችን የረጂም ጊዜ የእድገት ህልም ታሳቢ ያደረገ ሥራ ነው። ኅብረተሰቡ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ እና በእውቀቱ እንዲሳተፍ ይደረጋል። ወጣቶች የልማቱ ተጠቃሚ እንዲኾኑም የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
ሲጠናቀቅ መላ ኅብረተሰቡ የሚጠቀምበት እንዲኾን ተደርጎ መገንባቱ ልማቱን ሰው ተኮር ያደርገዋል ብለዋል ዶክተር አህመዲን።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!