
ባሕር ዳር: ኅዳር 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር ከተማን ለነዋሪዎች ምቹ፤ ለጎብኚዎችም ሳቢ ለማድረግ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ነው። ሥራውን ፈጥኖ በመጨረስ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በሌሊትም እየተሠራ ይገኛል።
የሌሊት ግንባታ ሥራውን የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አህመዲን ሙሀመድ (ዶ.ር)፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እና ሌሎችም የክልሉ እና የከተማዋ አመራሮች ጎብኝተውታል።
በጉብኝታቸው አስተያየታቸውን የሰጡት ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የኮሪደር ልማቱ በቀን በሦስት ፈረቃ እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰው በሌሊቱ ፈረቃ የሚሠሩት ሠራተኞች ለማበረታታት ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። በክልሉ በስምንቱም ሪጅኦፖሊታን ከተሞች ልማቱ እንዲሠራ አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው። በተለይ ደግሞ ጎንደር፣ ባሕር ዳር፣ ደብረ ብርሃን እና ደሴ ሥራዎች ተጀምረዋል። ሥራውን በፍጥነት ለማጠናቀቅ በቀን 16 ሰዓት እየተሠራ ነው፤ ከዚህ ውስጥም በምሽትም የሚሠራው ይገኝበታል ብለዋል።
በምሽት የመሥራት ፋይዳው ሥራውን በተቀመጠለት ጊዜ ለማጠናቀቅ፣ በጥራት ለመሥራት እና እግረ መንገዱንም የሥራ ባህላችንን ለማሳደግ መኾኑን ገልጸዋል። አመራር ማለት አስቸጋሪ ኹኔታዎችን ወደ ጥሩ አጋጣሚ የመቀየር ኃላፊነት ያለበት ነው ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ ያልተጠቀምንባቸውን ጸጋዎችም ወደ ልማት የመቀየር ኃላፊነትም አለብን ብለዋል። ባጋጠመን የሰላም ችግር ውስጥም ኾነን ማልማት ግድ ነው፤ በሁሉም አቅሞቻችን ተጠቅመን ልማትን እንሠራለን ነው ያሉት።
የጀመርናቸው የልማት ሥራዎች ከምንመኘው አኳያ አነስተኛ ቢኾኑም እንጋፈጣለን እንጂ የሰላም ችግሩን ምክንያት በማድረግ ከማልማት አንቆጠብም ነው ያሉት። በዚህ ወቅት ሥራውን በመጀመራችን የተፈጠረው የሥራ እድልም ቀላል አይደለም ብለዋል። ጎንደር ከ15 ሺህ በላይ እና በባሕር ዳርም በርካታ ሠራተኞች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት።
የኮሪደር ልማቱ የሥራ እድል በመፍጠር እና ሙያን በማሻሻል ለኅብረተሰቡ ጠቀሜታ እንዳለው ነው ርዕሰ መሥተዳድሩ የገለጹት። የፖለቲካ እና የጸጥታ መረጋጋትንም እንደሚፈጥር አክለው ገልጸዋል።
እንዲህ ዓይነቱን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ያለው ልማት በሌሊትም ቢኾን ተገንቶ ማበረታታት እንደሚገባ ገልጸዋል። ኅብረተሰቡም ሠላም የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር እና የዴሞክራሲ መሠረት መኾኑን እንዲረዳ ያሳሰቡት ርዕሰ መሥተዳድሩ በቤተሰብም ኾነ በማኅበረሰብ ደረጃ ለሰላም እንዲተጋ እና ልማቱን እንዲያግዝ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!