
ባሕር ዳር: ኅዳር 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ)ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የኾኑ አስፈጻሚ አካላት የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም መገምገም ዛሬ ተጀምሯል።
በግምገማው ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተቋም ግንባታ ማዕቀፍ በተሠራው ሪፎርም በርካታ የሀገር ሃብት ከሚባክንበት እና በየዓመቱ ኪሣራ ከሚመዘገብበት ታሪክ መውጣት ተችሏል ብለዋል።
በዚህም የሀገርን ኢኮኖሚ የሚደግፉ እና በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር በየዓመቱ ትርፍ የሚያስመዝግቡ፣ለበርካቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ ለዕዉቀት እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ ተቋማትን ፈጥረናል፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ በሆኑ ሁሉም ተቋማት የተጀመረዉ ሪፎርም ባለፉት ዓመታት የሚለካና የሚቆጠር ዉጤት አምጥቷል፡፡
በዛሬዉ መድረክ በዋናነት በመጀመሪያዉ ሩብ የበጀት ዓመት ለማሳካት ካቀድናቸዉ ጉዳዮች ዉስጥ ዋና ዋና አፈጻጸሞችን እንገመግማለን፡፡
በመሆኑም በተገቢው መንገድ ያሳካናቸዉን በማየት በጉድለት የታዩትንም በመንቀስ ፣ ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮችን በመለየት፣ የጋራ ርብርብ ለማድረግ በቀጣይ ለሚኖረን ምዕራፍ የተሻለ መነሳሳት የምንፈጥርበት መድረክ ይሆናል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!