
ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 3/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው የጸጥታ ችግር ምክንያት በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሕዝብ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ከፍተኛ ውድመት ደርሷል፡፡
እነዚህን ተቋማት በመጠገን እና መልሶ በመገንባት የተቋረጡ የሕዝብ አገልግሎቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መኾኑ ተገልጿል፡፡
አሚኮ ያነጋገራቸው የቢቸና ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌትነት በቀለ በተከሰተው ግጭት ምክንያት በከተማ አሥተዳደሩ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት ሕዝቡን በማስተባበር በማደስ እና በመገንባት አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ግጭቱን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በከተማ አሥተዳደሩ የእገታ እና የዝርፊያ ወንጀሎች ተበራክተው እንደነበር አስረድተዋል፡፡
አቶ ጌትነት ሕዝቡን በማስተባበር በተደረገ ክትትል እና እርምጃ በከተማዋ ይፈፀሙ የነበሩ የወንጀል ድርጊቶች መቀነሳቸውንም ተናግረዋል፡፡
የእነማይ ወረዳ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሥራ እና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አዲሱ ተሻለ በወረዳው በሚገኙ የአርሶ አደሮች ሠርቶ ማሳያ ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት መልሶ በመጠገን አርሶ አደሮች በተቋማቱ አገልግሎት እንዲያገኙ እና ምርታማ እንዲኾኑ ጥረት ሲደረግ እንደነበር እና ውጤት ስለመገኘቱም ነው የተናገሩት፡፡
የወረዳው ሕዝብ ግጭቱ ያስከተለውን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት በመገንዘብ ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እየጠየቀ ነው ያሉት አቶ አዲሱ ለተግባራዊነቱም የበኩሉን እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡
የሥራ ኀላፊዎቹ የታየው አንፃራዊ ሰላም ዘላቂነቱ እንዲረጋገጥ እና በግጭት ምክንያት የተስተጓጎሉ የልማት ተግባራት እንዲፋጠኑ ሕዝቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!