
ባሕር ዳር: ኅዳር 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር መብት አድማስ የድርጅታቸውን የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ የድርጅታቸው ያለፈው እና የተያዘው በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ውጤታማ እንደነበር ገልጸዋል። ችግሮችን ተቋቁሞ በመሥራት የመንገድ እና የድልድይ ግንባታ እንዲሁም የህንጻ ማደስ እና የስታድየም ፓርኪንግ ሥራዎች መሠራታቸውንም ጠቅሰዋል።
ከጉልህ ሥራዎቻቸው መካከልም አስቸጋሪ የነበረውን የተከዜ ድልድይ ግንባታ በ70 ቀናት ውስጥ ብቻ ማጠናቀቅ ችለናል ነው ያሉት። በዚህም የሰሃላ ሰየምት ወረዳን ሕዝብ ችግር መፍታት መቻሉን አንስተዋል።
ደሴ ከተማ ውስጥ የማሳለጫ ድልድይ እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የቢሮ እድሳትንም በፍጥነት እና በጥራት ሠርተው ማጠናቀቃቸውን ነው የገለጹት።
ከሥራዎቹም ወደ 1 ነጥብ 88 ቢሊየን ብር ገቢ እና 237 ሚሊየን ብር ትርፍ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሩም ሌላኛው የድርጅቱ ስኬት መኾኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል። ለ13 የተደራጁ ማኅበራት እና ለቀን ሠራተኞችም የሥራ እድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የወራቤ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ገንብቶ ለኅብረተሰቡ በማስረከብ እና የአቅመ ደካሞችን ቤት በመጠገን ማኅበራዊ ኀላፊነቱን ተወጥቷል ብለዋል።
በ2017 የሥራ ዘመንም ለውጤት እየተጋን ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ በክልሉም ከክልሉ ውጪም ሥራዎች ታቅደው እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል። ነባር እና አዳዲስ የመንገድ፣ የቢሮ እድሳት፣ የድልድይ ግንባታ ፕሮጀክቶችን እንሠራለንም ነው ያሉት።
በዚህ ዓመት ከ5 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ለመሥራት አቅደናል። ከነዚህም ውስጥ የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራ አንዱ ነው ብለዋል። ፕሮጀክቱንም በሁለት ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ ሌሊት ጭምር እየሠሩ መኾኑን አንስተዋል።
በሥራዎቻችን የድርጅታችን ገቢ ማሳደግ ብቻ ሳይኾን ፕሮጀክቶቻችን በፍጥነት አጠናቅቀን ለኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት ክፍት እናደርጋለን ነው ያሉት።
ድርጅቱ በአማራ ክልል ብቻ ሳይኾን በሀገር እና በአፍሪካ ደረጃም የመወዳደር አቅሙን ማሳደጉን ገልጸዋል። ለዚህም ከክልሉ ውጪ በሚሠሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች መሳተፉን እና በዩጋንዳም የፕሮጀክት ጨረታ በመሣተፍ ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ መኾኑን በአብነት ጠቅሰዋል።
ከክልሉ ውጪ የጀመርናቸው ከወራቤ – ሞጆ በር ያለውን የአስፋልት መንገድ እና የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ መንገድ ሥራ ፕሮጀክቶችን በማፋጠን እየሠራን ነውም ብለዋል።
ድርጅቱ ”ሕብር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን” በሚል ስያሜ በሕግ ወደ ኮርፖሬሽን እንዲያድግ ተወስኖ መደራጀቱ የተሻለ እንደሚሠራ እና ለክልሉም ትልቅ አቅም እንደሚኾን ዋና ሥራ አስኪያጁ በመግለጫቸው ተናግረዋል።
ትርፍ የሚገኘው በፍጥነት በመሥራት እና የሥራ ባህልን በማሻሻል ነው። ለዚህም ሌሊትም ጭምር እየሠራን ነው ብለዋል። የምንሠራው ለሕዝብ እና ለሀገር ስለኾነ በጥራት ላይ ድርድር የለንም ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ የጥራት ችግርንም ከተሻገርነው ቆይተናል ብለዋል። ድርጅቱ በውጤታማነቱም ተዓማኒነት እንዳተረፈ ገልጸዋል።
አቅማችን እያጠናከርን አትራፊ እና ለክልሉም የልማት አጋር መኾን እንፈልጋለን ያሉት ኢንጅነር መብት አድማስ ዘመኑ የውድድር ስለኾነ ፕሮጀክቶችን የምናገኛቸው ከዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች ጋር ተወዳድረን ነው ብለዋል። ግንባታዎቻችን በጥራት እና በፍጥነት በማጠናቀቅም ተወዳዳሪነታችን እና የሕዝብን ተጠቃሚነትም እናሳድጋለን ነው ያሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!