
አዲስ አበባ: ኅዳር 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኙነት፣ የዲሞክራሲያዊ አንድነት እና የሕገ መንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ባንችይርጋ መለሰ 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን አከባበርን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኅን ተቋማት መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ሕገ መንግሥታዊ ነው ያሉት ዋና ጸሐፊዋ ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቷን ያፀደቀችበት ዕለት መኾኑን ማስታወስ ያስፈልጋልም ብለዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት 1998 ዓ.ም በወሰነው መሠረት ሕገ መንግሥቱንም ለማሰብ የሚከበር በዓል መኾኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን ኢትዮጵያውያን የወል ትርክቶችን በማጎልበት አንድነታቸውን ለማጠናከር የሚጥሩበት እና ለሀገር ኅብረ ብሔራዊነት የሚሠሩበት እለት መኾኑንም ጠቁመዋል።
የበዓሉ መከበር ለረጂም ዘመናት ይዘውት የመጡት ትብብር በማጎልበት በማንነታቸው እንዲኮሩ የሚያደርግ ነው ያሉት የቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊዋ ዕለቱ ስለኅብረ ብሔራዊነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥስራዎች የሚሠሩበት መኾኑንም ጠቅሰዋል።
በዓሉ “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባምንጭ ከተማ ከኅዳር 24 አስከ ኅዳር 29/2017 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
ኅዳር 25 የወንድማማችነት ቀን፣ ኅዳር 26 የአብሮነት ቀን፣ ኅዳር 27 የደቡብ ኢትዮጵያ ቀን፣ ኅዳር 28 የምክከር ቀን እና ኅዳር 29 የኢትዮጵያውያን ቀን በሚሉ ስያሜዎች የየራሳቸው የአከባበር ሥነ ስርዓት ይኖራቸዋል ተብሏል።
ዋና ጸሐፊዋ 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን አንድነት እና ኅብረ ብሔራዊነት ሚዛኑን ጠብቆ እንዲሄድ በሚያስችል መልኩ ይከበራልም ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!