
አዲስ አበባ: ኅዳር 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ኪነ-ጥበብ እና ሥነ-ጥበብ ለሁለንተናዊ ልማት እና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ” በሚል መሪ ሃሳብ ከኪነ-ጥበቡ ዘርፉ ባለሙያዎች ጋር የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ ከዚህ ቀደም እንደ ሕዝብ ለሕዝብ ባሉ የሕዝቦችን እና የሀገራትን ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዞዎች ታላላቅ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ዓለም የኪነ-ጥበብ እና ሥነ-ጥበብ ዘርፉ ያለውን አቅም ተረድቶ በአግባቡ እየተጠቀመበት ነው ያሉት ሚኒስትሯ ኢትዮጵያውያን የዘርፉ ባለሙያዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ይህንን ልምድ መቅሰም እና መጠቀም ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ይህን መሰሉ ውይይት ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች ለመለየት እና መፍትሄውን በጋራ ለመፈለግ ዕድል የሚፈጥር ነው ያሉት ሚኒስትሯ ዘርፉ ያለውን ዕምቅ አቅም በጋራ ማልማት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ሚኒስትሯ የጥበቡን ዘርፍ ችግሮች በጋራ በመፍታት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ማዋል እንዲቻልም ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ታድመዋል። “የኪነ-ጥበብ እና ሥነ-ጥበብ ፈጠራ ለትውልድ ግንባታ እና ሁለንተናዊ ብልፅግና ያለው ፋይዳና የባለድርሻዎች ሚና” በሚል ርዕስ መነሻ ጽሑፍ ቀርቦም ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!