
ባሕር ዳር: ኅዳር 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በከተማዋ ግብርን በመሰብሰብ ረገድ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ስኬታማ ሥራ መሠራቱን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ የ2017 ዓ.ም “ግብር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ ሃሳብ የታክስ ንቅናቄ፣ የእውቅና እና ማበረታቻ መድረክ አካሄዷል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በበጀት ዓመቱ 8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ግብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በዚህ ሩብ ዓመት የከተማዋ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በቅንነት እና በታማኝነት በመክፈላቸው ስኬት ተመዝግቧል ብለዋል ።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የገቢ ተቋሙ ሙያተኞች እና መሪዎች በችግር ውስጥም ኾነው መስዋዕትነት እየከፈሉ ሥራቸውን በማከናዎናቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል ብለዋል።
ታማኝ ግብር ከፋዮች እና አገልጋዮች ባሉበት ከተማ ግብር የሚሰውሩ እና የሚያጭበረብሩ ግብር ከፋዮች ከምስጉን ግብር ከፋዮች መማር እንዳለባቸው ነው አቶ ጎሹ እንዳላማው የተናገሩት።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ኃይለማርያም እሸቴ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከግብር ከፋዮች 1 ቢሊዮን 682 ሚሊዮን 884 ሺህ 801 ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በዕውቅና አሰጣጥ መድረኩ ላይ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ክብረት ማሕሙድ እና ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ መሪዎችም ተገኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!