
ባሕር ዳር: ኅዳር 3/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንጅባራ ዙሪያ የሚገኙት አርሶ አደር የኔው ሙላት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብላቸው ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በደቦ እየሠበሠቡ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ለአጨዳ የደረሰን ሰብል ተሻምቶ ያልሠበሠበ አርሶ አደር እየጣለ ባለው ዝናብ ተጎድቷል ያሉት አርሶ አደር የኔው አሁን ላይ በተናጠል ሰብል የመሠብሠብ ሥራ ውጤቱ አጥጋቢ አለመኾኑን ተረድተው በአራት ቃዳ መሬት ላይ የለማን የጤፍ ሰብል በደቦ መሠብሠባቸውን አርሶ አደር የኔው ጠቁመዋል።
ሌላው በምሥራቅ ጎጃም ዞን የደጀን ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ታደለ መንግሥቱ “እኔ እና ቤተሰቦቼ የደረሰውን አዝመራ ለመሠብሠብ ብንሞክርም ዝናቡን መቅደም አልቻልንም። እናም በጎጥ እየተደራጀን ከጥዋት እስከ ምሽት በደቦ እየሠበሠብን ነው። በመኾኑም በስድስት ቃዳ መሬት ላይ የነበረ የገብስ፣ ባቄላ፣ አተር እና ጤፍ ሰብልን በሙሉ መሠብሠብ ችለናል” ነው ያሉት።
አርሶ አደር ታደለ በአደረጃጀት ሰብልን በደቦ በመሠብሠባቸው በእነርሱ ቀዬ አሁን ላይ ለብልሽት እና ብክነት የሚያሰጋ የሰብል ቁመና እንደሌለ ተናግረዋል።
በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የተንታ ጭርቆስ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት ወይዘሮ አንጓች እንየው በአራት ቃዳ መሬት ላይ ያለሙት የጤፍ ሰብል በደቦ መሠብሠቡን ነው የነገሩን። ኀብረተሰቡም በደቦ ማረስን፣ መሠብሠብን እና ወቅቶ ወደ ጎተራ ማስገባትን ተለማምዶታል ነው ያሉት።
ወይዘሮዋ “ልጄ ብቻውን ልሠብሥብ ቢል ኑሮ ዓመት ሙሉ የለፋንበት ሰብል ያለወቅቱ እየጣለ ባለው ዝናብ ይበላሽ ነበር” በማለት የደቦን ጠቃሜታ ተናግረዋል።
የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ የምርት ብክነት እንዳይኖር አርሶ አደሩ በደቦ ሰብሉን መሠብሠብ፣ መውቃት እና በጥንቃቄ ወደ ጎተራ እንዲያስገባ እየሠሩ እንደሚገኙ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ ታደሰ አስፋው (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ9 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የለማን የሰሊጥ እና ገብስ ሰብል ሙሉ በሙሉ መሠብሠብ መቻሉን የገለጹት ኀላፊው የአኩሪ አተር፣ የበቆሎ እና የጤፍ ምርትን ጨምሮ ሌሎች ሰብሎችም በአግባቡ እየተሠበሠቡ ነው ብለዋል
በተያዘው የምርት ዘመን በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም መምሪያ ኀላፊው ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በክልሉ በ2016/2017 የምርት ዘመን ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን አስታውሰዋል።
በማሳ ላይ ያለው የሰብል ቁመና ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያሉት ዶክተር ድረስ 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዶክተር ድረስ ዕቅዱ ዕውን እንዲኾን ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ ማድረግ የግድ ይላል ነው ያሉት።
በመኾኑም የክልሉ አርሶ አደር፣ የግብርና ባለሙያዎች እና መሪዎች እጅ እና ጓንት ኾነው የሰብል ሥብሠባ ሥራውን ባሕላዊ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እንዲያከናውኑ ነው ቢሮ ኀላፊው ያሳሰቡት።
የደረሰ ሰብልን ቀድሞ መሠብሠብ፣ የተሠበሠበን ሰብል ደግሞ መሬት ላይ ከማስጣት ይልቅ ከመሬት ከፍ አድርጎ መከመር እና የውቂያ ሥርዓቱም የምርት ብክነት በማያመጣ መንገድ መኾን አለበት ነው ያሉት።
በአማራ ክልል ሰሜን እና ማዕከላዊ ጎንደር፣ ምሥራቅ፣ ምዕራብ እና ሰሜን ጎጃም ዞኖች፣ አዊ እና ባሕርዳር ዙሪያ ወረዳ፣ በሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ ዋግ ኸምራ፣ ሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ አሥተዳደር ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!