የክልሉ ምክር ቤት የሕጻናት ፓርላማን የማጠናከር፣ የመደገፍ እና ልምድ እንዲቀስሙ የማድረግ ኀላፊነቱን ይወጣል፡፡

15

ባሕር ዳር: ኅዳር 2/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ዓለም አቀፍ የሕጻናት ቀንን በተለያዩ ክዋኔዎች እያከበረ ነው፡፡

ከሁነቶቹ መካከልም የፓናል ውይይት እና የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን መሸለም፣ ለሕጻናት ትኩረት ሰጥተው በመሥራት የተሻሉትን ዕውቅና የመሥጠት መርሐ ግብር አንዱ ነበር፡፡

በአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ አበራሽ ታደሰ በፓናል ውይይቱ ላይ የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በዓሉን ማክበሩን አመሥግነዋል፡፡ ለተማሪዎችም ድጋፍ መደረጉን አበረታትተዋል፡፡

በበዓሉ መሪ መልዕክት መሠረት ሕጻናት የሚሉትን አዳምጠናል፤ ሕጻናት ሊሟሉላቸው እና ሊጠበቁላቸው የሚገቡ ፍላጎቶች እና መብቶች እንዳሏቸው ተረድተናል ነው ያሉት፡፡

ለአካል ጉዳተኞች አመቺ ያልኾኑ መጸዳጃ ቤቶች፣ የውኃ እጥረት፣ የሥነ ልቦና ተጽዕኖ እና መሠል ችግሮች እንዳሉባቸው ስለመናገራቸውም ገልጸዋል፡፡

ስለዚህ ሁሉም ሕጻናት በጤንነት የመማር እና በደኅንነት የመኖር መብታቸው እንዲከበር ሁሉም ኀላፊነት አለበት ብለዋል፡፡

በውይይቱ ሕጻናት ኀላፊነትን መውሰድ እንዲማሩ እና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ አስተዋጽኦአቸውን እንዲያበረክቱ ልምምድ እያደረጉ ስለመኾኑ መገንዘባቸውን አስረድተዋል፡፡

ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ለሕጻናት መብት እና ክብር መጠበቅ የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። የተጀመረው ሥራም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ ብለዋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤትም የሕጻናት ፓርላማን በማጠናከር የመደገፍ እና ልምድ እንዲቀስሙ የማድረግ ኀላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል የሕጻናት ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሕጻን ተምኪን ይሀ ”ሕጻናት የሚሉት አላቸው፤ እናዳምጣቸው” በሚል መሪ መልዕክት ለሚከበረው የዓለም የሕጻናት ቀን እንኳን አደረሳችሁ ብላለች፡፡

ሕጻናት ከዕድሜያቸው ለጋነት የተነሳ ራሳቸውን ችለው ዘርፈ ብዙ ችግሮችን መፍታት አይችሉም፤ ይሁን እንጂ ተደራጅተው በመንግሥት፣ በኅብረተሰቡ እና መንግሥታዊ ባልኾኑ ድርጅቶች ድጋፍ ለውጥ ያመጣሉ ነው ያለችው፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ መሠረታዊ ሃሳብ በመነሳት ዓለማቀፋዊ እና አህጉራዊ ሕግጋትን በመቀበል አጽድቃ በመሥራት ላይ ትገኛለች ብላለች፡፡

ከዕድሜ፣ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ዝግጁነት ለጋነት ጋር በተያዘ ሕጻናት ካላቸው የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ባሻገር ይበልጥ እንክብካቤ እና ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ናቸው ነው ያለችው፡፡

አሠራሮችን በመዘርጋት የሕጻናት መብት እና ደኅንነት የሚያስጠብቁ መርሐ ግብሮችን በመንደፍ በሥነ ምግባር የታነጹ ሁለንተናዊ ስብዕና ያላቸው ተተኪ ትውልድ መፍጠር አስፈላጊ ነው ብላለች፡፡

በመኾኑም ሕጻናት በዚህ ቀን ተሳትፏቸው የሚጎለብትበት ከመኾኑ በተጨማሪ በመብት እና ደኅንነታቸው፣ በአሥተዳደግ እና አያያዛቸው ዙሪያ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ምክክር የሚደረግበት እና አቅጣጫ የሚቀመጥበት መድረክ ነው ብላለች፡፡

ዕለቱን ማክበር ያስፈለገበት ዐቢይ ዓላማም በሕጻናት መብቶች ላይ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ፣ የሕጻናትን ተሳትፎ ለማጎልበት፣ ባለልዩ ፍላጎት ሕጻናትን በትምህርት፣ በጤና ድጋፍ እና እንክብካቤ አገልግሎቶች ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ፣ ለችግር የተጋለጡ ሕጻናትን ድጋፍ ለማድረግ መኾኑን ጠቅሳለች፡፡

የሕጻናትን መብት እና ደኅንነት ማስጠበቅ የሚገባ በመኾኑ ኅብረተሰቡ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እንዲሁም ለሕጻናት የድርሻችን መወጣት ይገባናል የሚሉ ሁሉ የበኩላቸውን እንዲያግዙ ጥሪ አቅርባለች፡፡

በዕለቱ በ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ፈተናዎች የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል፡፡ ከጻናት ድጋፍ አኳያም የተሻለ ለሠሩ ተቋማት ውቅና እና ምሥጋና ተደርጓል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዘላቂ በኾነ መንገድ ተረጂነትን ለመቀነስ መንግሥት በዘንድሮው ዓመት ከፍተኛ በጀት መድቧል።
Next article“ደቦ” ወቅቱን ላልጠበቀ ዝናብ ችግር መፍቻ ቁልፍ!