
ደሴ: ኅዳር 2/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን የ2016 ዓ.ም እና የ2017 ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ ብሎም በቀጣይ ሥራዎቹ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቷል። በመርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉ የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሊ ሠይድ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ በመስኖ ልማት እና በቤተሰብ ጥሪት ግንባታ ዘርፍ ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የሴፍቲኔት ፕሮግራሙ በሰሜን ሸዋ ዞን በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጉን የዞኑ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አበባው መሠለ ተናግረዋል። በዞኑ 235 ሺህ ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ገልጸው ወደ 41 ሺህ የሚጠጉ ተጠቃሚዎችን በዚህ ዓመት ለማስመረቅ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ይህም ሲኾን ከተረጂነት አስተሳሰብ በመላቀቅ ቋሚ ገቢ ወደሚያገኙበት ሥራ በማሰማራት መኾኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም እንደ ዞን የአርሶ አደሮችን ሕይዎት ለመቀየር ታሳቢ በማድረግ የመስኖ ሥራ ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ነው ያብራሩት።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በዚህ ዓመት 12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለክልሉ መመደቡን ገልጸው ይህም እስከዛሬ ከነበረው ከፍተኛ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በክልሉ ወደ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሴፍቲኔት ተጠቃሚ መኖሩን የተናገሩት ኮሚሽነሩ በዚህ ዓመት ወደ 196 ሺህ አባዎራዎች እንደሚመረቁም ተናግረዋል።
ሲመረቁም ዘላቂ በኾነ መንገድ ራሳቸውን እንዲችሉ ብድር መመቻቸቱንም ነው ያስረዱት።
የመጨረሻው የሴፍቲኔት ፕሮግራም ዓላማ ተጠቃሚዎች ሃብት እና ጥሪት ፈጥረው እንዲመረቁ ማድረግ ቢኾንም ከዚህ አንፃር ግን ድክመት መኖሩ ተገምግሟል ብለዋል።
ፕሮግራሙ ማኅበረሰቡን ተረጂነትን እና ጥገኝነትን በማለማመዱ ይህንን አስተሳሰብ ለማላቀቅ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ማኅበረሰቡ ከድህነት የሚወጣው በማምረት እንጂ በእርዳታ አለመኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) “ዘላቂ በኾነ መንገድ ተረጂነትን ለመቀነስ በመንግሥት በኩል ቁርጠኛ አቋም በመኖሩ በዘንድሮው ዓመት በትኩረት ሥራዎች ይከናወናሉ” ብለዋል።
ተረጅነትን ከመቀነስ አኳያ በክልሉ ላለፉት 20 ዓመታት ከ43 ቢሊዮን ብር በላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ከፍተኛ ሥራ ሢሠራ መቆየቱን ተናግረዋል።
ዘላቂ በኾነ መንገድ ተረጂነትን ከመቀነስ አኳያም መንግሥት በዘንድሮው ዓመት ከፍተኛ በጀት መመደቡንም ጠቅሰዋል።
ይህም ሲኾን በሴፍቲኔት የታቀፉ ወረዳዎች በአግባቡ ይህንን በጀት ተጠቅመው የተሻለ ለውጥ እንዲያመጡ በማለም መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- መስዑድ ጀማል
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!