የጎንደር የልማት እና ሰላም ማኅበር (ጎልሰማ) በጎንደር እና አካባቢው ሰላም እንዲሰፍን እየሠራ ነው።

35

አዲስ አበባ: ኅዳር 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ጎልሰማ” በጎንደር እና በአካባቢው ያለውን እምቅ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ሃብት በመለየት፤ የማኅበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ተግዳሮት የኾኑትን የሰላም እና የልማት ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት “ሰላምን ማስፈን፣ ልማትን ማፋጠን ይቻላል” በሚል መርህ የሚመራ ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋም ነው።

ማኅበሩ ቀጣይነት ያለው ልማት ብሎም ዘላቂ ሰላም በጎንደር እና አካባቢው እንዲሰፍን እየሠራ እንደኾነ የጎንደር የልማት እና ሰላም ማኅበር (ጎልሰማ) ጠቅላላ ጉባኤ ሠብሣቢ ፈቃደ አበበ ገልጸዋል።

ሠብሳቢው የጎንደር ተወላጆችን፣ ወዳጆችን በማስተባበር እና በልዩ ልዩ ዘርፎች በማደራጀት ለአማራ ብሎም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም እና ሁለንተናዊ ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለ ማኅበር ነው ብለዋል።

ማኅበሩ የያዘውን ዓላማ ለማሳካት የጎንደር እና አካባቢውን ሕዝብ ልማት እና ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የሰላም አስተምህሮ፣ የመልካም አሥተዳደር እና የሀገር ግንባታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የባሕል እና ታሪክ አስተምህሮ፤ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እሳቤን ማሳደግ እና የአጋርነት ግንባታ ተግባራትን ማከናወን መሠረት አድርጎም እየተንቀሳቀሰ መኾኑን ሠብሣቢው አንስተዋል።

በማኅበሩ በ2015/16 ዓ.ም የተከናወኑ ተግባራት ቀርበው ውይይት ተደርጓል።

በማኅበሩ የተከናወኑ ተግባራትን የገለጹት የማኅበሩ ጸሐፊ ኢንጅነር በሪሁን ካሳሁን የማኅበራቱን ውህደት ሕጋዊ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል፡፡

ማኅበሩ ለመምህራን እና ለትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች የትምህርት አመራር ሥልጠና መስጠት እንዲሁም በሰባት የትምህርት አይነቶች የተዘጋጁ ከ550 በላይ አጋዥ መጽሐፍትን እና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ ብሎም የስርጭት ሥራ መሥራቱን ተናግረዋል።

ኢንጅነር በሪሁን ማኅበሩ ከተቋቋመ ጀምሮ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ መቻል እና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በተፈጥሮ አደጋ እና በድርቅ ለተጎዱ ድጋፍ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል።

የጎንደር ልማት እና ሰላም ማኅበር (ጎልሰማ) በጎንደር አካባቢ ተወላጆች እና ደጋፊዎች ሲንቀሳቀሱ የቆዩ የጎንደር መልሶ ማቋቋም እና ልማት ማኅበር (ጎልማ) እና የጎንደር ሰላም እና የዕድገት ማኅበር (ጎ-ሰ’ማ) የተባሉ የሲቪክ ማኅበራትን በማዋሃድ የካቲት 18/2015 ዓ.ም በጎንደር ከተማ የተቋቋመ ማኅበር ነው።

የጎንደር የልማት እና ሰላም ማኅበር (ጎልሰማ) የ2016 ዓ.ም ዕቅድ አፈፃፀም እና የቀጣይ ዕቅድ ላይ ውይይት በአዲስ አበባ አካሂዷል።

ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለሕጻናት የሚያደርገውን ድጋፍና እንክብካቤ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
Next articleዘላቂ በኾነ መንገድ ተረጂነትን ለመቀነስ መንግሥት በዘንድሮው ዓመት ከፍተኛ በጀት መድቧል።