ለሕጻናት የሚያደርገውን ድጋፍና እንክብካቤ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

35

ባሕር ዳር: ኅዳር 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኅዳር 11 ዓለም አቀፍ የሕጻናትን ቀንን በተለያዩ ሁነቶች እያከበረ ነው። ከሁነቶቹ መካከልም የፓናል ውይይት አንዱ ነው። በፓናል ውይይቱ ከክልሉ ዞኖች የተወከሉ ሕጻናት እና የክልል ተቋማት ኀላፊዎች እና ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ተሳታፊ ሕጻናት ሃሳብ እና ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲኾን ዋና ዋናዎቹ:-
👉 በግጭት ምክንያት ለትምህርት ማቋረጥ እና ለስደት እየተዳረግን ነው።
👉 የተስፋፋው ሕጻናት እገታ የመማር፣ የመጫዎት እና የነጻነት መብትን እየገደበ ነው። እገታን አስቁሙልን፤ የጸጥታ ኃይሉ ሰላሙን ያስከብርልን።
👉 ቤተ መጻሕፍት እና የጊዜ ማሳለፊያዎች እንዲሁም በዞን መሥሪያ ቤቶች የሕጻናት ማቆያ የለም እና ቢታሰብበት፣
👉 የትምሕርት ግብዓት ውድነት በሕጻናት ትምህርት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው፤ የሚደረገው ድጋፍም በቂ አይደለምና ድጋፉ ቢሰፋ፣
👉 ለተፈናቃይ ተማሪዎች የሚደረገው ድጋፍ ጥሩ ቢኾንም አሁን ላይ መቀዛቀዝ ይታይበታልና ይጠናከር፣
👉 ሊስትሮ እና ሌሎች ሥራዎች እየሠሩ የሚማሩ ሕጻናት አሉና ድጋፉ ተጠናክሮ ቢቀጥል፣
👉 የአይሲቲ ትምህርት ግብዓቱ ባለመኖሩ ሕጻናት ተገቢ ትምህርት እያገኘን አይደለም፣
👉 ቢቲንግ የሚባለው የቁማር ጨዋታ በመፈቀዱ የሕጻናትን ሕይወት እየተበላሸ መኾኑን ታውቆ ቢስተካከል የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

በውይይቱ የተገኙት የመሥሪያ ቤቶች ኀላፊዎች እና ተወካዮች ሕጻናቱ ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጥያቄዎቹ ትክክል መኾናቸውን አምነው መንግሥት እየሠራባቸው እና የኅብረተሰቡ ትብብርም እንደሚያስፈልግ ነው ያነሱት።

የኢኮኖሚ ችግር ላለባቸው ልጆች በተቋማት የነጻ እና የቅድሚያ አገልግሎት የሚያገኙበትን አሠራር በመተግበር ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የቤቲንግ ቁማር ቤቶችን በተመለከተ ሥልጣኑ የፌዴራል መንግሥት መኾኑ ነው የተገለጸው። ነገር ግን ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግሮ እልባት ይሰጥበታል ነው የተባለው።

የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የተነሱ ሃሳቦች እና ጥያቄዎች ትክክል መኾናቸውን ገልጸው ለጥያቄዎቹ መለስ እና ለችግሮች መፍትሄ ቢሯቸው ከሚመለከተው ተቋም ጋር እየተመካከረ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ሕጻናት በአዕምሮ ዳብረው እና በደኅንነት በማደግ ሀገር ተረካቢ እንዲኾኑ እንሠራለን፤ በችግር ውስጥ የሚገኙ ሕጻናትን ችግሮች ለመቅረፍም አቅማችንን አስተባብረን ጥረት እናደርጋለን ነው ያሉት።

በአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ በምክር ቤቶች የሕጻናትን ተሳትፎ እና ሚና ለማሳደግ እንሠራለን ብለዋል።

ከማኅበራዊ እና ከምጣኔ ሃብት ልማት አኳያም ምክር ቤቱም ትኩረት ሰጥቶ በመገምገም የሕጻናትን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ህጻናትን ለሱስ ተጋላጭ የሚያደርጉ የንግድ ድርጅቶች እና ግለሰቦችን በመቆጣጠር እና ሁኔታዎችን በማመቻቸት በሕጻናት ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ እንሠራለን ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቱሪዝም ዘርፉንም ለማዘመን በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ላይ እንግዶችን የሚመራ አፕሊኬሽን ተሠራ።
Next articleየጎንደር የልማት እና ሰላም ማኅበር (ጎልሰማ) በጎንደር እና አካባቢው ሰላም እንዲሰፍን እየሠራ ነው።