የቱሪዝም ዘርፉንም ለማዘመን በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ላይ እንግዶችን የሚመራ አፕሊኬሽን ተሠራ።

45

አዲስ አበባ: ኅዳር 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የስፔስ ሳይንስ እና የጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላቸው ፀሐይ በስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ዘርፍ የክልሎችን አቅም በማሳደግ እና ልማትን በማፋጠን በራሳቸው የሚሠሩበትን አቅም ለመፍጠር እየተሠራ እንደኾነ ገልጸዋል።

በቴክኖሎጂ ዘርፍም በኢንስቲትዩቱ የለሙ ለሥራ ዕድል ፈጠራ በተለይም ለወጣቶች የሚያግዙ በኮምፒውተር የሚሠሩ ማሽኖች እንደሚተላለፉ እና ክልሎችን በባለቤትነት መጠቀም የሚያስችል የሳተላይት ዳታ የመሠረተ ልማት ዝርጋታም እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ከሁሉም ክልሎች ጋር በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት እንደታቀደ የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቤቴልሄም ንጉሴ አስረድተዋል፡፡ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ታዳጊዎችን በቴክኖሎጂው ዘርፍ ወደፊት እንዲመጡ የማድረግ እና በቀጣይነትም ወጣቶች በራሳቸው የሥራ ዕድል የሚፈጥሩበትን መንገድ እስከማመቻቸት ይሠራል ብለዋል። የቱሪዝም ዘርፉንም ለማዘመን በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ላይ እንግዶችን የሚመራ አፕሊኬሽን መሠራቱን ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ከተሞች እና መሠረተ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሱለይማን እሸቱ በአገልግሎት አሰጣጥ ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ከመፍታት እና አሠራርን ከማዘመን አኳያ ከተሞች በፕላን እንዲመሩ እና ዘመናዊ የመሬት አሥተዳደር ሥርዓት የሰፈነባቸው እንዲኾኑ ለማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ስለመኾናቸው ነው የተናገሩት፡፡

ይህን ውጤታማ ለማድረግ ከቴክኖሎጂ ጋር ትስስር ካላቸው ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት ወሳኝ እንደኾነም አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የዜሮ ደረጃ የምድር መቆጣጠሪያ ነጥብ መገንባት፣ የመጀመሪያ ደረጃ የምድር መቆጣጠሪያ ነጥብ ግንባታ እና ለከፍታ ማዘመን የሚረዳ የከፍታ ልኬት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ የምድር መቆጣጠሪያ ነጥብ ግንባታ ንባብ መውሰድ ከክልሎች ጋር በ2017 ዓ.ም በጋራ የሚሠሩ ዝርዝር ሥራዎች መኾናቸው ተጠቅሷል፡፡

ለአየር ፎቶ ማስተካከያ የሚኾን የቅድመ በረራ ምልክት ማስቀመጥ፣ የምድር መቆጣጠሪያ ነጥቦችን በባለቤትነት ማሥተዳደር እና የ”ሲኦአርኤስ” ተከላ መሥራት እንዲሁም የዞን፣ የወረዳ እና የቀበሌ ወሰን እና የቦታ ስም መረጃ ማደራጀት በበጀት ዓመቱ በጋራ እና በተናጠል የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው፡፡

ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ሴቶች ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለህጻናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
Next articleለሕጻናት የሚያደርገውን ድጋፍና እንክብካቤ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።