
ባሕር ዳር: ሕዳር 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ ከሃይማኖት አባቶች ጋር የሰላም ውይይት እየተካሄደ ነው። በመድረኩ ላይ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ተገኝተዋል። የመድረኩ ዓላማ በጎንደር ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ታላላቅ የሃይማኖት አባቶች ጋር ስለወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ለመመካከር ነው።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው “ጎንደር የእምነት እና አብሮ የመኖር እሴት ባለቤት፤ የአርቆ አሳቢ አባቶችም መገኛ ናት” ብለዋል። ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ታላላቅ መካሪ አባቶች ባሉበት ምድር ይፈጸማል ተብሎ የማይጠበቅ፣ የጎንደርንም ክብር የማይመጥን የጸጥታ ችግር መስተዋሉንም ገልጸዋል።
ነገ ለልጆቻችን የምትመች ሀገር የምናሻግረው ዛሬ ቁርሾ ባለመፍጠር ነው፤ የተፈጠሩ ስህተቶችን በጥልቅ አስተውሎት መገንዘብ እና የከተማዋን ሰላምም በዘላቂነት መመለስ አለብን ሲሉ አሳስበዋል። በጎንደር እና አካባቢው ብሎም በአማራ ክልል የገጠመውን የሰላም ችግር ለመፍታት የሃይማኖት አባቶች ሚና የጎላ ድርሻ እንደሚኖረውም አስገንዝበዋል። ከአባቶች ጋር በመመካከር ለሕዝባችን የሚበጅ ዘላቂ ሰላም እንፈጥራለን ነው ያሉት።
ጎንደር የቀደመ ታሪኳ ለሀገር የሚበጅ ጥልቅ ሃሳብ ማመንጨት፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ እምነት እና እሴትን መጠበቅ እና ሀገር መሥራት ነው፤ ዛሬም አፍራሽ ተግባር ላይ የተሰማሩትን በመምከር ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት ከንቲባው። የሃይማኖት አባቶች በየቤተ እምነቶቻቸው ስለሰላም ዋጋ በማስተማር ዘላቂ ሰላም እና የተረጋጋች ሀገር በመመሥረት ሂደት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ የሃይማኖት አባቶችም ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት እንደኾ አንስተዋል። የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ለሀገር እና ለሕዝብ የማይበጅ በመኾኑ ሁሉም ለሰላም እና ለውይይት በአንድነት መቆም እንዳለበት አስገንዝበዋል።
አሁን የታየው ሰላም ዘላቂ እንዲኾን፣ የጎንደርን የቆየ ታሪክ የሚያጎድፍ ድርጊትም እንዳይደገም የጋራ ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል። መላው የሃይማኖት አባቶችም በየቤተ እምነቶቻቸው ተከታዮቻቸውን ስለሰላም ማስተማር እንዳለባቸው ገልጸዋል። አጥፊዎችንም በአባታዊ ሥርዓት መምከር እንደሚገባ የውይይቱ ተሳታፊ አባቶች አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!