ለገንዘብ ሲባል ወገንን ማሰቃየት የተገባ ነውን?

13

ባሕር ዳር: ኅዳር 2/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰው ኋላ ከመጣ ገንዘብ ይልቅ አብረውት የኖሩት ወገን አይሻልምን? ሲቸግር የሚጠሩት፣ ሲከፋ ድረስ የሚሉት ወገን አይበልጥምን? ለገንዘብ ሲባል ወገንን ማሰቃየት የተገባ ነውን? ለገንዘብ ሲባል ወገኖች በሰላም ወጥተው በሰላም እንዳይገቡ ማድረግ ጤነኝነት ነውን?

በስዎች ስቃይ መደሰት፣ ድሃን ማስለቀስ፣ እናትን ከልጆቿ መነጠል፣ አረጋውያንን ያለ ጧሪ ማሳጣት ጭካኔ አይኾንምን? ለዓመታት የደከሙበትን ንብረት ዘርፎ መውሰድስ እንደ ነውር አይደለምን? ለራሳቸው ሳይጎርሱ ሌሎችን የሚያጎርሱ፣ ለራሳቸው ሳይለብሱ ሌሎችን የሚያለብሱ፣ ራሳቸው እየተጠሙ ሌሎችን የሚያጠጡ ደጋግ ባሉባት ምድር ኬሎች ጉረሮ ጉራሽ መንጠቅ የተገባ ነውን?

በክፉ ዘመን መደጋገፍ ሲገባ መነቃቀፍ፣ በችግር ዘመን መጠባበቅ ሲገባ መጠቃቃትስ ነውር አይኾንምን? የገበያ ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ አበው በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የእገታ፣ የቅሚያ፣ የዘረፋ እና ሌሎች ወንጀሎች እንዲበራከቱ አድርጓል፡፡ ከእናታቸው እቅፍ ካልወጡ ሕጻናት እስከ አረጋውያን ድረስ ይታገታሉ፡፡ ታፍነው ገንዘብ ይጠየቅባቸዋል፡፡ መክፈል የሚችሉ ወገኖች ያሏቸው የታገቱትን ገዝተው ይመልሷቸዋል፡፡ መክፈል የማይችሉ ግን ድጋሜ ላያዩዋቸው በሃዘን ይሰናበቷቸዋል፡፡

ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በትራንስፖርት የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ስጋት አለባቸው፡፡ አሽከርካሪዎች በየቦታው ገንዘብ ይጠየቃሉ፡፡ ተጓዦች ይንገላታሉ፤ ሃብት እና ንብረታቸውን ይቀማሉ፡፡ በከተሞች በምሽት የሚንቀሳቀሱ ንጹሐን እየተስፈራሩ ሃብታቸውን ይነጠቃሉ፡፡ ወይንም ታግተው ወደ ማይታወቅ ሥፍራ ይወሰዳሉ፡፡ ነዋሪዎች በነጻነት ወጥተው አይገቡም፡፡

ሠርተው የሚበሉ ወገኖች ጫናው በዝቶባቸዋል፡፡ እንደ አሻቸው በሰላም አይንቀሳቀሱም፡፡ የሚቀማቸው፣ የሚያግታቸው እና የሚዘርፋቸው አለና፡፡ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ አንድ ባለታሪካችን ተወልደን ባደግንበት ከተማ በሰላም ወጥቶ መግባት አደጋ ኾኖብናል ይላሉ፡፡ የሚቀማው እና የሚዘርፈው በዝቷል ነው የሚሉት፡፡

የገጠማቸውን ሲነግሩን “ከሰሞኑ ምሽት አንድ ሰዓት ከመኾኑ አስቀድሞ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከጓደኞቼ ጋር እንሄድ ነበር፡፡ ወቅቱ አስቀድሞ የሚጨልበት በመኾኑ ጨልሟል፡፡ መብራት ጠፍቷል፡፡ ዝናብም ይዘንብ ነበር፡፡ እየሄድን እያለ ሦስት ሰዎችን አገኘን፡፡ ሁለቱ ማሰሪያ ይዘዋል፡፡ አንደኛው ደግሞ በትር ይዟል፡፡ እኛ የጸጥታ ኀይሎች ናቸው ብለን ነበር፡፡

ቁሙ ብለው አስቆሙንና ያላችሁን አውጡ አሉን፡፡ እንዳንሮጥ መሳሪያ ከያዙት አንደኛው ከጀርባችን ቆመ፡፡ ከፊት ለፊታችን መሳሪያ ከያዙት አንደኛውና ዱላ የያዘው ቆመዋል፡፡ ምንም ማድረግ አልቻልንም የያዝነውን ሁሉ ሰጠናቸው” ነው ያሉት፡፡ ባለታሪካችን እንደነገሩን ቀምተው ዝም አላሉንም፡፡ እኔን መቱኝ፡፡ ከዛ በኋላ ከአጠገባቸው በፍጥነት እንድንርቅ አባረሩን ነው የሚሉት፡፡ ዘረፋና ቅሚያ ተበራክቷል፡፡ በምሽት የተገኘ ይቀማል፡፡

አንዳንዶቹ ዝም ብለው አይቀሙም፤ መቀማታቸው ሳያንስ ይማታሉ፣ ወይም በጩቤ ይወጋሉ ነው ያሉት፡፡ ከዘራፊዎች እና ከቀማኞች ራስን ለመጠበቅ ኅብረተሰቡ በአንድነት እርስ በእርሱ መጠባበቅ ይገባል ብለዋል፡፡ በተለይም በከተሞች በመደራጀት ሠፈርን መጠበቅ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሠፈራቸውን እየጠበቁ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ነዋሪዎች ራሳቸውን በራሳቸው መጠበቅ ካልቻሉ የጸጥታ ኀይሎች በሁሉም አካባቢ መድረስ እንደማይችሉም ተናግረዋል፡፡ ማኅበረሰቡ በሰቀቀን ነው የሚኖረው ያሉት ባለ ታሪካችን የጸጥታ ችግሩን ምክንያት በማድረግ ዘረፋ በዝቷል ነው ያሉት፡፡ እየኖርን ያለነው በምሬት ነው፤ ለማን እንናገር እያልን ነው ብለዋል፡፡

ሌቦችን እና ዘራፊዎችን አጋልጦ ለመስጠትም ዋስትና አጥተናል ነው የሚሉት፡፡ ጊዜው እስኪያልፍ እና መደበኛ የሕግ አገልግሎት እስኪመጣ ድረስ ራስን በራስ መጠበቅ ይገባል ብለዋል፡፡ ነዋሪዎች በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ እና መኖር የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባል ነው ያሉት፡፡ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ክፍል ኀላፊ ምክትል ኮማንደር መሳፍንት እሸቴ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተለያዩ ወንጀሎች ሲፈጸሙ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ወንጀሎች ደግሞ በኅብረተሰቡ ውስጥ ብዙ ጉዳቶችን አስከትለዋል ነው ያሉት፡፡ የእገታ፣ የቅሚያ፣ የዘረፋ እና ሌሎች ወንጀሎችን ለመከላከል የጸጥታ ኀይል ስምሪቱን የማስተካከል ሥራ መሥራታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከጸጥታ ኀይሉ ስምሪት ባለፈ የሕዝቡ ድጋፍ እና ትብብር ምን መኾን መቻል አለበት በሚለው ጉዳይ ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡ የጸጥታ ኀይሉ እና የሕዝቡ ቅንጅታዊ አሠራር በማደጉ ብዙ አካባቢዎች ለውጥ እየታየ ነው ብለዋል፡፡ ከተሞች ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ ያለው ሥራ መልካም መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ከተሞች ላይ የጸጥታ ተቋማት ከሚያደርጉት ጥበቃ ባለፈ ኅብረተሰቡ አካባቢውን እንዲጠብቅ እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ማኅበረሰቡ አካባቢውን ሲጠብቅ እና የጸጥታ ኀይሉ ዋና ዋና በሮችን ይዞ ቁጥጥር እና ስምሪት ሲያደርግ ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት፡፡ ነገር ግን አሁንም የሚፈጸሙ ወንጀሎች አሉ ብለዋል፡፡

ገንዘብ ለማግኘት ሲባል የሚፈጸሙ ወንጀሎች መኖራቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሰዎች ወደ አልተገባ የወንጀል ድርጊት እንዲገቡ እያደረጋቸው መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ከመጥፎ ልምምድ መራቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አሁንም ምክክር እና ውይይት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ማስፋት፣ የወንጀል ምርመራ ሥራዎችን በጥንካሬ መስጠት ይገባል ነው ያሉት፡፡

አካባቢን የመጠበቅ እና የማደራጀት ጉዳይ በትኩረት ሊሠራበት ይገባል ብለዋል፡፡ የሕግ ማስከበር ሥራውም ተጠናክሮ መቀጠል መቻል አለበት ነው ያሉት፡፡ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ለውጦች እየታዩ የመጡት በሕዝቡ ትብብር መኾኑን ያነሱት ኀላፊው አሁንም ከዚህ የተሻለ መሥራት ይገባል፣ በኅብረተሰቡ ዘንድም ጥሩ መነሳሳት እየተፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

ማኅበረሰቡ ከጸጥታ ኀይሎች ጋር በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅበትም አንስተዋል፡፡ ከሕዝብ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ወንጀልን ለመከላከል አያደረገው ያለው ድጋፍ የጸጥታ ኀይሉ የሚሠራውን ሥራ እንደሚያቀልለትም ተናግረዋል፡፡ መደማመጥን እንደ መውጫ መንገድ መጠቀም አለብን ያሉት ኀላፊው መሳሳብ እና አለመደማመጥ ለዚህ ችግር ዳርጎናል፤ ከመሳሳብ ወጥቶ በመደማመጥ መሥራት ይገባል ነው ያሉት፡፡

መሳሳብ እና የመነዳት ፖለቲካ ዋጋ እያስከፈለ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ሕግ እና ሥርዓትን የተከተለ ሥራ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ሥርዓት አልበኝነትን መለማመድ እንደማይገባም አስገንዝበዋል፡፡ ሰከን ብሎ ማሰብ ሕግ እና ሥርዓትን ማክበር ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባለፉት 18 ዓመታት በብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ኅብረ ብሔራዊነት ላይ የተሻለ ግንዛቤ ተፈጥሯል።
Next articleየሃይማኖት አባቶች ለከተማዋ ሰላም የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው አሳሰቡ።