
ባሕር ዳር: ኅዳር 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የግጭት መንስዔዎች እና የዘላቂ ሰላም ግንባታ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው። አውደ ጥናቱ የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ከአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።
በአውደ ጥናቱ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉደዮች አሥተባባሪ እና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው፣ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን፣ የአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አባተ ጌታሁን (ዶ.ር) ጨምሮ ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
በአውደ ጥናቱ መልእክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው የአማራ ክልል ሕዝብ ለሀገራዊ ለውጡ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ኾኖ የታገለ፣ ሀገር አሁን ላለችበት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ደረጃ ከፍተኛ ድርሻ ያለው መኾኑን ተናግረዋል።
በለውጡ እንደ ሀገር የፖለቲካ ምሕዳሩን በማስፋት፣ የዲሞክራሲ ባሕል እንዲጎለብት፣ ብዝኀነትን በማስተናገድ እሴቶች እንዲያድጉ፣ ኅበረ ብሔራዊ ሥርዓተ መንግሥት እውን እንዲኾን ትልቅ ዋጋ ተከፍሏል ነው ያሉት። በአማራ ክልል ዋጋ ያስከፈሉ እና እያስከፈሉ ያሉ ጉዳዮች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
ሃሰተኛ ትርክት፣ የሰሜኑ ጦርነት፣ ከድኅረ ጦርነት በኋላ የአሥተዳደር ችግር፣ የጸጥታ ኃይሎች መልሶ ማደራጀት ሂደት እና አፈጻጸም፣ ይህንን ተከትሎ የተበተነው የጦር መሳሪያ አሥተዳደር ችግር ክልሉን እንደጎዱት አመላክተዋል።
የማኅበረሰቡ ወርቃማ እሴቶች እየተሸረሸሩ መምጣት፣ ብዝኀነትን የማስተናገድ ጉድለት እና ፖለቲካዊ አውዱ ውድቀት ምክንያት ሕዝብ ለጸጥታ ችግር ተጋልጧል ነው ያሉት። በክልሉ ያለውን የሰላም እጦት በመፍታት ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባናል ብለዋል።
የክልሉ ሕዝብ በሚገባው ልክ ተጠቃሚ ለማድረግ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በክልሉ ለተፈጠረው ጥልቅ ችግር ጥልቅ ጥናት እና ጥልቅ መፍትሄ ያስፈልገዋል ነው ያሉት። የክልሉን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የሚያስችል ጥናት መጠናቱንም ተናግረዋል። ጥናቱን ላጠኑትም ምሥጋና አቅርበዋል። የአማራ ክልል ሕዝብ በደርሻው ልክ በኢትዮጵያዊነቱ በልማት፣ በዲሞክራሲ፣ በሰላም ተጠቃሚ እንዲኾን እንደሚሠራም ገልጸዋል። ሕዝቡ አሁን ከገባበት የጸጥታ ችግር እንዲወጣ ከፍ ያለ ኀላፊነት መወሰዱንም ተናግረዋል። የክልሉ ሕዝብ ከችግር እንዲወጣ ከግለሰባዊ ጥቅም ባለፈ በሕዝብ ተቆርቋሪነት መንፈስ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!