
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር መክሯል።
የምክክር መደረኩን የመሩት የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ችግሮቻችንን መፍታት ያቃተን፣ በክብራችን ልክ ያልተገኘነው፣ ወደ ታች የተመለስነው፣ ነውርን ነውር ባለማለታችን ነው ብለዋል። ኀላፊው ግጭቱ የክልሉን ሕዝብ እየጎዳ እንጂ እየጠቀመ አለመኾኑንም ተናግረዋል።
ግጭቱ ተማሪዎች እንዳይማሩ፣ እናቶች በጤና ተቋማት እንዳይወልዱ፣ በድህነት የተሠሩ ተቋማት እንዲወድሙ እያደረገ ነው ብለዋል።
ለሕዝብ የሚቆረቆር ከተሞች ላይ ቦንብ እያፈነዳ፣ ሕዝብን አያሸብርም ነው ያሉት። በገበያ እና በትምህርት ቤት ላይ ቦንብ በማፈንዳት የሕዝብን ጥያቄ ማስፈታት እንደማይቻልም ገልጸዋል።
ሕጻናትን የሚያግትን፣ ንብረት የሚዘርፍን እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይኖር የሚያደርግን ኀይል መደገፍ እንደማይገባም ተናግረዋል።
ጽንፈኛ ኀይሉ ሽማግሌዎችን እና የሃይማኖት አባቶችን የሚያዋርድ መኾኑንም ገልጸዋል። መንግሥትን በኀይል ማፍረስ እንደማይቻልም ተናግረዋል።
“ክልሉን ወደ ዝቅታ ያወረድነው ሁላችን ተባብረን ነው” ያሉት ምክትል ኀላፊው የድርሻችንን ወስደን ሁኔታውን ለመቀየር መሥራት አለብን ብለዋል። ከሀሰት ትርክት መውጣት እና ስለ ኢትዮጵያዊነት ማቀንቀን እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ለሚኖረው የአማራ ሕዝብ የሚያስብ ሁሉ ስለ ኢትዮጵያዊነት ማቀንቀን ይገባዋል ብለዋል። ከታላቅነት መውረድ እንደማይገባም ገልጸዋል።
መንግሥት ለሰላም ዝግጁ መኾኑን የተናገሩት ምክትል ኀላፊው ለሰላም ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን መሥራቱንም አብራርተዋል።
ጽንፈኛ ቡድኑ ግን ለሰላም ዝግጁ አለመኾኑን እና ለሰላም የሚሠሩ ሰዎችን እንደሚያንገላታ ነው የተናገሩት። ከጠላት ጋርም አብሮ እየሠራ ነው ብለዋል። ከጠላቶች ጋር አብሮ የሚሠራውን ኀይል በጋራ መታገል ይገባል ነው ያሉት።
ባለሀብቶች እንዳይሠሩ፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይኖር፣ ኢኮኖሚው እንዲወሳሰብ፣ ግብር እንዳይሠበሠብ፣ የልማት ሥራዎች እንዳይሠሩ እና ክልሉ እንዲወድም እያደረገ ነው ብለዋል።
ሁላችንም በአንድነት ችግሮችን መፍታት ይጠበቅብናል ነው ያሉት። ሕዝቡ በቃ ሊለው እንደሚገባም ተናግረዋል።
ቡድኑ እያገተ፣ እየዘረፈ እና እያሸበረ እንዲኖር መፍቀድ እንደማይገባም ገልጸዋል። በጋራ ኾኖ መታገል እና ችግሮችን መፍታት እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!