“ኢኮኖሚያዊ አቅምን ለማሳደግ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል” ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን

81

ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር መክሯል።

በምክክሩ የተገኙት የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን ስለ ሰላም ከንድፈ ሃሳብ ባሻገር ያሉ ተጨባጭ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

በክልሉ ለተፈጠረው ቀውስ ድርሻ የሌለው አካል እንደሌለ ያመላከቱት ኮሚሽነሩ ችግሩን ለመፍታት ውሥብሥብ የኾነው ብዙ አካላት ስለተሳተፉበት ነው ብለዋል።

በክልሉ ነውር የኾኑ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የሕዝብ በደል እየጨመረ እንዲሄድ ያደረገው ዋናው ጉዳይ ብዙ አካላት የሚሳተፉበት በመኾኑ ነው ብለዋል።

እነዚህ አካላት እጃቸውን ቢሠበሥቡ ሕዝቡ በአጭር ጊዜ ሰላሙን ማረጋገጥ እንደሚችልም አንስተዋል። በክልሉ በተፈጠረው ችግር ለይቶላቸው በዘረፋ እና በቅጥፈት የሚጠቀሙ ኀይሎች ብቻ ሳይኾኑ በተጓዳኝ የሚጠቀሙ ኀይሎች መኖራቸውን ነው ያመላከቱት። እንዲህ አይነት ችግሮች ደግሞ ችግሩን ለመፍታት እያወሳሰቡት መኾናቸውን ነው የገለጹት።

ሁላችንም የችግሩ ባለቤቶች ነን ብለን ማመን አለብን ያሉት ኮሚሽነሩ አርሶ አደሮች የሚያመርቱት ምርት ወደ ገበያ እየቀረበ አይደለም፣ የልማት ሥራዎችም እየተጓተቱ ነው ብለዋል።

በእንዲህ አይነት አካሄድ በሀገር አቀፍ ደረጃ በኢኮኖሚ እና በሌሎች ዘርፎች ተወዳዳሪ ለመኾንም አስቸጋሪ እንደሚኾን ነው የተናገሩት።

ሰላም የሌለው ኅብረተሰብ እና አካባቢ ስለ ልማት ማሰብ ይከብደዋል ነው ያሉት። ኢኮኖሚያዊ አቅምን ለማሳደግ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ያሉት ኮሚሽነሩ በየቦታው ግጭት እና ጦርነት ካለ ወደ ልማት የሚገባ አለመኖሩን አመላክተዋል። የጸጥታ ኀይሉ ሰላምን ለማረጋገጥ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

ሕዝቡ መረጃዎችን ለጸጥታ ኀይሉ እየሰጠ መኾኑን የተናገሩት ኮሚሽነሩ የሚደርሰውን መረጃ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።

አስነዋሪ የእገታ ወንጀሎች ይፈጸማሉ፣ ሰውን ሰው እየሰረቀ፣ እያገተ ገንዘብ እየጠየቀ አስነዋሪ ተግባር እየተፈጸመ ነው ብለዋል። ይሄን አስነዋሪ ተግባር ለመቅረፍ በጋራ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።

የሃይማኖት አባቶች ምዕመናን መምከር እና ማስተማር ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። ያልተገቡ መልዕክቶችን ከማስተላለፍ መቆጠብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ሰላማዊ ውይይቶችን እያሰፉ መሄድ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጤና ተቋማት ጥራቱን የጠበቀ የላብራቶሪ አገልግሎት እንዲሠጡ ማስቻል የኢንስቲትዩቱ ዋና ሥራ መኾኑን አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ አስገነዘቡ፡፡
Next article“በገበያ እና በትምህርት ቤት ላይ ቦንብ በማፈንዳት የሕዝብን ጥያቄ ማስፈታት አይቻልም” የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር)