
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የኅብረተሠብ ጤና ኢንስቲትዩት 3ኛውን የጤና ላብራቶሪ ፌስቲቫል “ጥራት ያለው የላብራቶሪ አገልግሎት ለማይበገር የጤና ሥርዓት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
በዚህ ፌስቲባል ላይ የአማራ ክልል ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ተገኝተዋል፡፡ ዋና አፈ ጉባኤዋ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከተቋቋመበት ዋና ዋና ዓላማዎች ውስጥ አዳዲስ በሽታዎችን በፍጥነት መለየት፤ የምርምር እና የሪፈራል ላብራቶሪ ማዕከል ኾኖ ማገልገል፤ እንዲሁም ባለድርሻ እና አጋር አካላትን በማስተባበር ዘመናዊ እና ጥራት ያለው የላብራቶሪ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
የጤና ተቋማት ጥራቱን የጠበቀ የላብራቶሪ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ እንዲሠጡ ማስቻል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ሥራ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡
በሁሉም የጤና ተቋማት ጥራት ያለው የላብራቶሪ አገልግሎት እንዲኖር የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ ቀጣይነት ያለው የጤና ላብራቶሪ ልማት እንዲኖር ኢንስቲትዩቱ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በየዓመቱ በተከታታይ ከዕውቅና ሰጭ ተቋማት በሚደረገው ቁጥጥር እና ቅኝት እንደ ሀገር ሙሉ ዕውቅና በማግኘት ያስቀጠለ ተቋሞ በመኾኑ ዕውቅና ሊሰጠው እንደሚገባም ዋና አፈ ጉባኤዋ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!