“ከታሪክ ተወቃሽነት ለመውጣት ተረባርቦ ክልሉን ከችግር ማዳን ይጠበቃል” ምክትል ኮሚሽነር እንየው ዘውዴ

49

ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር መክሯል።

በምክክሩ የተገኙት የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ገደቤ ኃይሉ የአማራ ክልል በብዙ ነገር የታደለ፣ ለልማት፣ ለቱሪዝም እና ለሌሎች ሥራዎች የተመቼ መኾኑን ገልጸዋል።

ክልሉ የፈለገውን አምርቶ መለወጥ የሚችል እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ ያለው መኾኑንም ተናግረዋል። በክልሉ የታጣው ሰላም መኾኑንም ነው የገለጹት። ክልሉ ያለው ጸጋ እና ሃብት በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት እየወደመ መኾኑንም ተናግረዋል።

የአማራ ሕዝብ ከአብራኩ በወጡ ሥልጣን እና ገንዘብ ናፋቂ ጽንፈኛ ኀይሎች እየሞተ፣ ንብረቱ እየወደመ ነው ብለዋል። የአማራ ሕዝብ ችግሮቹን በውይይት መፍታት የሚችል ብልሕ መኾኑንም ገልጸዋል። ሕዝብን እያስቸገሩ ያሉ ኀይሎችን ተው ማለት እና በድፍረት መታገል ይገባልም ብለዋል።

ንጹሐንን የሚያግተውን፣ ንብረት የሚቀማውን፣ የሚዘርፈውን ኀይል ማስታገስ የሚቻለው በመታገል መኾኑንም ተናግረዋል።

ሕዝብን ለስቃይ እየዳረገ ያለውን ኀይል በድፍረት ማውገዝ እና መታገል ካልተቻለ ችግሩ በሁሉም ቤት ይገባል ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶች ብሎም የሀገር ሽማግሌዎች መምከር እና በሰላም እንዲገቡ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል። ሕዝብን ለሚዘርፉ ኀይሎች ድጋፍ የሚያደርጉትን እረፉ ማለት ይጠበቃል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እንየው ዘውዴ ለዘላቂ ሰላም የሕዝብ ድጋፍ እና ትብብር ያስፈልጋል ነው ያሉት። ያለ ሕዝብ ተሳትፎ የሚረጋገጥ ዘላቂ ሰላም እንደማይኖርም ተናግረዋል።

ሰላም የሁሉም መሠረት መኾኑንም አመላክተዋል። በሰላም እጦት የደረሰውን ችግር የገፈቱ ቀማሽ ሕዝብ እንደሚያውቀውም ገልጸዋል።

እየጠፋ ያለው የሰው ሕይወት፤ እየወደመ ያለው ንብረት ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ የመጨረሻው መቋጫ ውይይት ነው ብለዋል።

በተፈጠረው ችግር ምክንያት የአማራ ክልል ከሌሎች ክልሎች ጋር እኩል ለመኾን ብዙ ጊዜ እንደሚወስድበትም ተናግረዋል።

ማኅበረሰቡን እያማረሩ ያሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ማስተካከል፣ ሕዝብን እየበደሉ ያሉትን ደግሞ ማጽዳት ይጠበቃል ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ትውልድን የሚቀይሩ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል። ከታሪክ ተወቃሽነት ለመውጣት ተረባርቦ ክልሉን ከችግር ማዳን ይጠበቃል ነው ያሉት።

ከሕዝብ እሴት እና ባሕል ያፈነገጡ ኀይሎችን በጋራ መታገል ይገባልም ብለዋል። የሰዎችን መታገት ዝም ብሎ ማየት እንደማይገባም ገልጸዋል። ሁሉም በየአቅሙ መሥራት ከቻለ ችግሩን መፍታት ይቻላል ነው ያሉት።

ማኅበረሰቡ ልጆቹ ከትምህርት ቤት ቀርተውበት፣ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እየደረሱበት በመኾኑ በምሬት ላይ መኾኑን የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ አብዛኛው የኅበረተሰብ ክፍል ሰላም ፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል። ሰላም እንዲመጣለት በምሬት እየጠየቀ መኾኑንም አንስተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመንግሥት ተቋማት የከተማ ግብርና ተሞክሮ ማሳያ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ።
Next articleበደብረሲና ከተማ የእየተሠሩ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የሥራ እድል በመፍጠር ውጤታማ መኾናቸው ተገለጸ።