የመንግሥት ተቋማት የከተማ ግብርና ተሞክሮ ማሳያ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ።

76

ደብረማርቆስ: ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት በሀገር አቀፍ ደረጃ በምግብ ራስን ለመቻል እየተከናወኑ የሚገኙ ጥረቶችን ከማሳካት ባለፈ የማኅበረሰቡን የአመጋገብ ሥርዓት ለማሻሻል ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ተገልጿል።

በምሥራቅ ጎጃም ዞን የጎዛምን ወረዳ አሥተዳደር በ2016 የክረምት ወቅት በወረዳው ባሉ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚገኝ 3 ሄክታር መሬት ለጥቅም ያልዋለ መሬትን በተለያዩ ቋሚና ጊዜያዊ ተክሎች አልምቶ ለመንግሥት ሠራተኞች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የወረዳው ዋና አሥተዳዳሪ ሙሉሰው ቀሬ ተናግረዋል።

መሬት ጾም ማደር የለበትም በሚል ተነሳሽነት በተከናወነው የተቋማት የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት የመንግሥት ተቋማትን ገጽታ በመቀየር መሥሪያ ቤቶች የከተማ ግብርና ተሞክሮ ማሳያ እንዲኾኑ ማድረግ መቻሉን ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል።

የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማቱን ከንብ እርባታ እና ከሌሎች የእንስሳት ሃብት ልማት ጋር በማስተሳሰር “ምግቤን ከጓሮየ” የሚለውን አሠራር በማስረጽ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የሚያስችል ተግባር እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት።

የወረዳው ዋና አሥተዳዳሪ በቀጣይ ሰላምን በማረጋገጥ የልማት ተሞክሮዎችን በየቀበሌው ባሉ አርሶ አደሮች እና በሌሎች የመንግሥት ተቋማት ለማስፋት ጥረት እንደሚደረግ አስገንዝበዋል ።

በተቋሙ ግቢ ለልማት ያልዋለን ሰፊ መሬት ወደ ልማት መቀየሩ ምቹ የሥራ ድባብ እንዲፈጠርላቸው ማድረጉን የወረዳው የመንግሥት ሠራተኞች ተናግረዋል። ልማቱ ራስን በምግብ ለመቻል ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መኾኑንም ገልጸዋል።

በቀጣይም በመሥሪያ ቤቱ በሚሠሩ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ንቁ ተሳታፊ በመኾን በአትክልት እና ፍራፍሬ የበለጠ ተጠቃሚ ለመኾን ስለመዘጋጀታቸው ተናግረዋል።

ከጊዜያዊ አትክልት በተጨማሪ ዘላቂ ጥቅምን ለማረጋገጥ 2 ሺህ 500 የቡና፣ 1ሺህ የአኘል፣ 1ሺህ 500 የአቡካዶ፣ 1ሺህ 250 የማንጎ እና ሌሎች ቋሚ ችግኞች መተከላቸው ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደቡብ ወሎ ዞን ኩታበር ወረዳ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።
Next article“ከታሪክ ተወቃሽነት ለመውጣት ተረባርቦ ክልሉን ከችግር ማዳን ይጠበቃል” ምክትል ኮሚሽነር እንየው ዘውዴ