
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ የኅብረሰብ ክፍሎች ጋር መክሯል።
በውይይቱ የተገኙ ተሳታፊዎች ግጭትን የሚጠላ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ ይገባል ብለዋል። “ለሰላም ምን ያክል ፍላጎት አለን?” ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ነው ያሉት። ግጭትን መጥላት እና ለሰላም ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ይገባል ብለዋል። ሁላችንም ለሰላም ዝግጁዎች ብንኾን በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ከአንድ ዓመት በላይ አይሻገርም ነበር ነው ያሉት።
ችግር ለሚፈጥሩ ኃይሎች ምሽግ የኾንናቸው እኛው ነን ብለዋል። ሁሉም ሰላም ፈላጊ ከኾነ የክልሉን ሰላም በአጭር ጊዜ መመለስ እንደሚቻልም ገልጸዋል። ችግሩን የሚፈታው ትጥቅ ሳይኾን የሕዝብ አንድነት እና መተባበር ነው ብለዋል።
መሪዎችም ለሕዝብ አገልጋይ መኾን እንደሚገባቸው የተናገሩት ተሳታፊዎቹ መሪዎች አንድነትን በማጠናከር ችግሮችን መፍታት እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
የሃይማኖት አባቶች ፖለቲካን ከሃይማኖት ሳይቀላቅሉ ስለ ሰላም መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል ተሳታፊዎች። የሀገር ሽማግሌዎችም በታማኝነት የማስታረቅ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል። ሰላም የሚመጣው በውይይት እና በምክክር መኾኑንም አመላክተዋል። ችግሮቻችን በውይይት እና በሽምግልና የመፍታት ባሕላችንን ማሳደግ አለብን ነው ያሉት።
ሰላም የሌለው ሀገር ዕድገት፣ ዴሞክራሲ እና ልማት እንደማይኖረው ገልጸዋል። ሰላምን ከራስ መጀመር እንደሚገባም ተናግረዋል።
ሰላም የሚመጣው ለሰላም በሰራነው ልክ ነው ብለዋል። የችግሩ ባለቤቶችም፣ የችግሩ ተጎጂዎችም፣ የችግሩ መፍትሔ አምጪዎችም እኛው ነን ነው ያሉት። የሰላም እጦት እያስከተለ ያለውን ችግር ከሌሎች መማር እንደሚጠበቅም ገልፀዋል። ከግጭት የሚተረፍ ነገር አለመኖሩንም አመላክተዋል።
ስለ ሰላም ከመናገር ባሻገር ስለ ሰላም መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት። በክልሉ እየኾነ ያለው የፀጥታ ችግር የሚያሳዝን እና የማይጠቅም፤ የክልሉን ሕዝብ በእጅጉ እየጎዳ መኾኑንም ተናግረዋል።
የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን ካልተወጣ ጉልበታሞች ሕዝብን ለስቃይ እንደሚዳርጉት ነው የገለጹት። የእስካሁኑ ችግርና መከራ ይበቃናል ነው ያሉት። ሁሉም አካል በትብብር፣ በአንድነት፣ በመተሳሰብ መሥራት እንደሚገባውም ገልጸዋል።
የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት በክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ የግጭት መከላከልና አፈታት ዳይሬክተር መንግሥቱ ፈረደ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ለማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች መዳረጉን ነው የተናገሩት። ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ደኅንነትን፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ በሕዝብ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መልካም ምላሽ መስጠት፣ አድሎዓዊ አሠራርንና ሙስናን ማጥፋት፣ የአገልግሎት አሠጣጥን ማሻሻል ይገባዋል ነው ያሉት።
የሃይማኖት ተቋማት ለተከታዮቻቸው መንፈሳዊ ሕይወትን መገንባት፣ ሰላምና ፍቅርን ማስተማር አለባቸው ብለዋል።
የሀገር ሽማግሌዎችም ከአድሎአዊነት ራሳቸውን በማራቅ መምከር እና ማስታረቅ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ወጣቶች ስሜታዊ ከኾኑ እርምጃዎች መውጣትና ማመዛዘን አለባቸው ብለዋል። የሌሎች ድብቅ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ከመኾን መቆጠብ፣ ከተሳሳቱ መረጃዎች ራስን ማራቅ፣ ሀገርን ለመረከብ በሥነ ልቡና፣ በእውቀት እና በአካል ዝግጁ መኾን፣ ለሕግ የበላይነት ተገዥ መኾን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ሴቶችም ለሰላም ግንባታ ከፈተኛ ድርሻ እንዳላቸውም ተናግረዋል። ሴቶች ያላቸውን ማኅበራዊ ኃላፊነት ተጠቅመው መምክርና ማስተካከል ይገባቸዋል ብለዋል።
ሚዲያንም በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል። የሚዲያ አጠቃቀም ጥንቃቄ ካልተደረገበት ከሕግ ልዕልና መጣስ፣ ለሰብዓዊ መብቶች መጣስ እና ለሌሎች ችግሮች እንደሚዳርግ ነው የተናገሩት። ሚዲያው የሰላም ድልድይ ኾኖ መሥራት አለበት ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነትን በውይይት እና በሰለጠነ መንገድ የመፍታት ባሕልን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው ነው የተናገሩት። ግጭትን እንደ ፖለቲካ ግብዓት መጠቀም እንደማይገባም ገልጸዋል። የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ለሰላም የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል።
ከግጭትና ከጦርነት በመውጣት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ከሁሉም እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!