
አዲስ አበባ: ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 15ኛው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ጉባኤ በአፍሪካ ኅብረት እየተካሄደ ነው።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ 15ኛው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የሚኒስትሮች ጉባኤ ለአህጉሪቱ ዘላቂ ልማት እና አዲሲቷን አፍሪካ በአዲስ ገጽታ የሚያስተዋውቅ ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ በንግዱ ዘርፍ አፍሪካን እርስ በእርስ በማስተሳሰር ኢኮኖሚዋ የማይናወጥ አህጉር ለመገንባት በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ለአህጉሪቱ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህንን የንግድ ትስስር ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የፓን አፍሪካ ጥራት ማረጋገጫ ኢንስቲትዩት ሊቀ መንበር ሄነሪ ሮቲች (ዶ.ር) የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማሳለጥ ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን ለዓለም ገበያ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና በኩል የጥራት ማረጋገጫ የወጣላቸው ምርቶች እንዲመጡ እና ዓለም አቀፉን ገበያ እንዲቀላቀሉ ፖሊሲ ወጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!