“በአርሶ አደሮች የሚነሳውን የትራክተር ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየሠራን ነው” የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳድር

99

ደሴ: ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳድር ከ84 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የገዛቸውን የማረሻ ትራክተሮች ለወረዳዎች አስረክቧል።

የእርሻ ትራክተር ከተረከቡት ወረዳዎች መካከል የመቅደላ እና ወረኢሉ ወረዳዎች ይጠቀሳሉ። የወረዳዎቹ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሠይድ አደም እና ጌታቸር ተስፋየ ወረዳዎቹ ለትራክተር እርሻ ምቹ መኾናቸውን ገልጸው ትራክተሮቹን በውጤታማነት በመጠቀም ምርትን ለማሳደግ እንሠራለን ብለዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አህመድ ጋሎ በዞኑ ከ4 መቶ 32 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለእርሻ የዋለ መኾኑን ገልጸዋል። ከዚህም 35 ከመቶ የሚኾነው ለትራክተር እርሻ ምቹ መኾኑን ነው የተናገሩት። በዞኑ በቂ ትራክተር አለመኖሩን ያነሱት መምሪያ ኀላፊው ከ2015 ጀምሮ በተሠራ ሥራ 39 የእርሻ ትራክተሮችን ለተለያዩ ወረዳዎች ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል። በዛሬው እለት ርክክብ የተደረገባቸው 12 ትራክተሮች ከ84 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገባቸውም አስረድተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮነን እንደገለጹት የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው።

በአርሶ አደሮች የሚነሳውን የትራክተር ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የገለጹት ዋና አሥተዳዳሪው በቀጣይም ለአርሶ አደሮች የመውቂያና የማጨጃ ትራክተሮችን ተደራሽ ለማድረግ እንሠራለን ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ሕይወት አስማማው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ደሴ ከተማ የቱባ ባሕል ባለቤት እና የኢትዮጵያ የቅርስ ማዕከል በመሆኗ እንደ ስሟ መልማት ይገባታል” የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“የአፍሪካን ልማት እና ብልጽግና ለማረጋገጥ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ወሳኝ ነው” ታየ አጽቀሥላሴ