
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ በመንግሥት እና በኅብረተሰብ ተሳትፎ ለሚሠራዉ የኮሪደር ልማት ከአካባቢዉ ባለሃብቶች ጋር የገቢ ማሰባሰብ መርኃ ግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነዉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳድር ምክትል ከንቲባና የደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት አስተባባሪ ዣንጥራር ዓባይ በበኩላቸዉ ደሴ እንደ ቀደምትነቷ መልማት ይገባታል ፣ ይህንን ልማት የመደገፍ ኃላፊነት ደግሞ የሁላችንም ነዉ ብለዋል።
በመርኃ ግብሩ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአብሮነትና የመቻቻል ተምሳሌት የሆነችዉን ደሴ ከተማን ለማልማት የመጣችሁ ምሥጋና ይገባችኋል ብለዋል።
ደሴ ከተማ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም ማልማት ያስፈልጋል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የተጀመረው የደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት የዚህ አንዱ አካል መኾኑን አንስተዋል።
ደሴን ማልማት የክልሉን ሃብት ይብልጥ መደገፍ መኾኑን ያስገነዘቡት ርእሰ መሥተዳድሩ በዚህ ታሪካዊ ተግባር ሁሉም እንዲሳተፍ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት መንገድ ፣ የታክሲ ተርሚናሎች ፣ የመዝናኛ ቦታዎች ፣ በከተማዋ የሚያልፈዉን የቦርከና ወንዝ ተከትሎ የወንዝ ዳርቻ መሰረተ ልማት ፣ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን ያካተተ መኾኑም ተጠቅሷል። ይህንን የኮሪደር ልማት ለማጠናቀቅ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግም በመርኃ ግብሩ ተነስቷል።
ዘጋቢ፦ኤልሳ ጉዑሽ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!