
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የኅብረተሠብ ጤና ኢንስቲትዩት 3ኛውን የጤና ላብራቶሪ ፌስቲቫል “ጥራት ያለው የላብራቶሪ አገልግሎት ለማይበገር የጤና ሥርዓት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
ለአንድ ሀገር የጤና አገልግሎት ሥርዓት ውጤታማነት ጥራት ያለው የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎት መስጠት ወሳኝ እንደኾነ በፌስቲባሉ ተገልጿል።
የጤና ተቋማት ጊዜው የሚጠይቀውን ዘመናዊ የላቦራቶሪ መመርመሪያ መሳሪያዎችን እና የሠለጠኑ ባለሞያዎችን በመጠቀም ትክክለኛ የምርመራ ውጤት በአጭር ጊዜ በማውጣት ጥራት ያለው የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎት ለማኅበረሰቡ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ነው የተባለው።
የአማራ ክልል የኅብረተሠብ ጤና ኢንስቲትዩት በክልሉ ለሚገኙ የጤና ተቋማት የላቭራቶሪ ጥራት ቁጥጥር ሥራዎችን በመተግበር ውጤታማ ሥራ እየሠራ እንደኾነም ተገልጿል፡፡
ኢንስቲትዩቱ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ ክትትል እና ድጋፍ እንዲሁም የማሻሻያ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ በማድረግ የክልሉን የላቦራቶሪ አገልግሎት ለማሻሻል እና ጥራቱን ለማረጋገጥ ጠንክሮ እየሠራ እንደሚገኝ ነው ያሳወቀው።
የፌስቲቫሉ ዓላማም በክልሉ አገልግሎት እየሠጡ ያሉ ላብራቶሪዎችን የምርመራ ጥራት እና ቅልጥፍናን በመዳሰስ ብሎም በመለየት ከጥንካሬያቸው እና ከክፍተቶቻቸው ትምህርት መውሰድ እንዲችሉ ለማስቻል እንደኾነ ተብራርቷል፡፡
በላብራቶሪ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከሚሳተፉ አጋር አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሠራርን ማሳደግ እና የጋራ መግባባትን መፍጠር እንደሚገባም ነው የተገለጸው፡፡
የላብራቶሪ ግብዓት አቅራቢዎችን እና የሚመለከታቸውን አካላት በማገናኘት አዳዲስ የላብራቶሪ አገልግሎቶችን በኢግዚቪሽን ማስተዋወቅ ብሎም በላብራቶሪ አገልግሎት የተሻለ አፈፃፀም ላላቸው ተቋማት እና አካላት ዕውቅና መስጠት ታሳቢ ያደረገ ፊስቴቫል ስለመኾኑም ነው የተጠቆመው።
በፊስቲቫሉ ላይ የአማራ ክልል ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ፣ የአማራ ክልል የኅብረተሠብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ፣ የኢትዮጵያ የሕክምና ላብራቶሪ ማኅበር ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አስቴር ፀጋየ እና የአርማወር ሀንሠን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ተገኝተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!