
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከተቋማት የቢሮ ኃላፊዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከወጣቶች እና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየመከረ ነው።
በምክክር መድረኩ የአማራ ክልል ሴቶች ፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ብርቱካን ሲሳይ፣ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጀንን ጨምሮ የቢሮ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ወጣቶች ተገኝተዋል።
በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ክልሉ ከነበረበት የጸጥታ ችግር ተሻግሮ ወደ ተሻለ ሰላም በመሸጋገር ላይ መኾኑን ተናግረዋል። ከአንድ ዓመት በፊት ሰዎች እንደ ልብ የማይንቀሳቀሱበት እንደነበር የተናገሩት ምክትል ኃላፊው አሁን ላይ ሁኔታው ተቀይሮ ያሰብነውንና ያቀድነውን የምናሳከበት ሁኔታ ተፈጥሯል ነው ያሉት።
ውይይቱ ለሰላም ከእያንዳንዳችን የሚጠበቀውን ለመለየት እና ኃላፊነት ለመውሰድ ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል። ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው ሰላም ከጤና፣ ከምንተነፍሰው አየር፣ ከምንመገበው ምግብ ተለይቶ አይታም ነው ያሉት ። ሰላም የልማት እና የአብሮነት መሠረት ነው ብለዋል። ሰላም የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅም አመላክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!