
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በባሕርዳ ከተማ አሥተዳደር ሰባታሚት ቀበሌ ነዋሪዎች ጋር የሰላም ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ የተገኙ ነዋሪዎች ዘላቂ ሰላምን እንሻለን ብለዋል፡፡ መንግሥት ሰላምን የማረጋገጥ ኃላፊነትን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡ ሁሉም ለሰላም መሥራት እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል፡፡ በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች ለሕዝብ በቂ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም፤ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ሕዝብን እያማረረ ነው ብለዋል፡፡
ከማንም በላይ ሰላም እንፈልጋለን ያሉት ነዋሪዎቹ ፤ በሁሉም በኩል ያለው ችግር ካልተፈታ ሰላም ሊመጣ እንደማይችልም አመላክተዋል፡፡ ዘረፋና ቅሚያ ተበራክቷል ይበቃናል ነው ያሉት፡፡ የሰላም እንቅፋት የኾኑ ኃይሎችን ከሁሉም በኩል ማጽዳት ይገባል ብለዋል። ለሰላም የተግባር ሥራ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
በውይይቱ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ የአካባቢ ሰላም ማስከበር ዋና ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ዘሪሁን አስራደ “ከእኔ በላይ ላሳር በሚል አስተሳሰብ ብዙ ችግሮች ደርሰዋል” ብለዋል፡፡ በሰላም እጦት ምክንያት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች ውስጥ ገብተናል ነው ያሉት፡፡ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖር፣ ተማሪዎች እንዳይማሩ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
ሕዝብን እየጎዱ ያሉ አስተሳሰቦችንና ግጭቶችን መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡ በግጭት ምክንያት የሥራ እድል የፈጠሩ ፋብሪካዎች መዘጋታቸውንም አስታውሰዋል፡፡ በአማራ ሕዝብ ስም የተነሳው ኃይል ራሱን በማበልጸግ ላይ ነው ብለዋል፡፡ ለሰላም የከፈልነው ዋጋ አነስተኛ በመኾኑ ምስቅልቅል ውስጥ እንድንገባ ኾኗል ነው ያሉት፡፡ በአልተገባ አካሄድ የሀገር ኩራት የኾነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስም እንዲጠለሽ ኾኗል፤ ለሀገርና ለሕዝብ የማይጠቅሙ ድርጊቶች ተፈጽመዋል ብለዋል፡፡
ነዋሪዎቹ እስካሁን የደረሰውን ጉዳት ታሳቢ በማድረግ የአካባቢያቸውን ሰላም መጠበቅ እንደሚገባቸውም አመላክተዋል፡፡ ለሀገር ሰላም አንደኛው ሟች ሌላኛው ተመልካች መኾን እንደማይገባውም ገልጸዋል፡፡ ሰላምን በማጽናት ዜጎች በሰላም ሠርተው የሚኖሩበት አካባቢ ሊፈጠር ይገባል ነው ያሉት፡፡
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊና የከንቲባ ተወካይ ጤናው ምህረት፤ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ለማስፈታት እርስ በእርስ መገዳደል እንደማይገባ አመላክተዋል፡፡
እስካሁን ያለው አካሄድ የአማራን ጥያቄዎች የማያስመልስ፣ እድገቱን የሚያቀጭጭ አውዳሚ አካሄድ ነው ብለዋል፡፡ ወጣቶች ለሰላም ዘብ መኾን እንደሚገባቸውም አመላክተዋል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን እየመከሩ ለሰላም እንዲገቡ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል፡፡ የመማር ማስተማር ሂደት ማስተጓጎል ተገቢ አለመኾኑንም አመላክተዋል፡፡
የምሥራቅ ዕዝ ገርባሳ ማሠልጠኛ ማዕከል ምክትል አዛዥና ተወካይ ሥልጠና ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ደሳለው ኪሮስ ሰላም ወዳዱ ሕዝብ ሰላም በማይፈልጉ ኃይሎች በችግር ውስጥ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ ሕዝቡ ሰላም ካለ ሠርተን እንበላለን፤ ልጆቻችን ይማራሉ፤ የተሻለ ገቢ ይኖራል እያሉ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ በኃይልና በአመጽ የሚመለስ ጥያቄ ስለሌለ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ለማስመለስ መሥራት ይገባል ነው ያሉት፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚዋጋው የሕዝብን ሰላም ለማስጠበቅ እንጂ ሐሰተኞች እንደሚሉት በሕዝብ ላይ የተነሳ አይደለም ብለዋል፡፡ ሠራዊቱ ሥነ ምግባር ያለው፣ ከራስ በላይ ሕዝብና ሀገርን የሚያስቀድም፣ ለሕዝብ ሰላም የሚሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በሕዝብ ስም የሚምሉና የሚገዘቱ ኀይሎች የራሳቸውን ሃብት እያካበቱ እንጂ ለሕዝብ የሚጠቀም ሥራ እየሠሩ አይደለም ብለዋል፡፡
“ሰላም ያልወደደና ወደ ሠራዊቱ የሚተኩስን ኃይል አከርካሪውን የመስበር ሥራችን አጠናክረን እንቀጥላለን” ነው ያሉት፡፡ እስካሁን ድረስ ያልጠራው ሃሳብ እንዲጠራ ትዕግሥት ተደርጓል ያሉት ሌትናል ኮሎኔሉ ንጹሐንን እየለየ ጥፋተኞችን የማጽዳት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ ለሰላም ከተዘጋጀ ኃይል ጋር በሰላም እንሠራለን፤ መዋጋት የሚፈልግ ደግሞ ከንጹሐን ተለይቶ መምጣት አለበት ነው ያሉት፡፡
ለአማራ የሚታገል አማራን አይገድልም፤ አማራን አይዘርፍም፤ የእርሻ በሬውን አያርድም፤ አግቶ ብር አይቀበለውም ብለዋል፡፡ ተሳስተው ወደ ጥፋት መንገድ የገቡ ሰላምን በመምረጥ ወደ ሰላም መመለስ አለባቸው ነው ያሉት፡፡ ለሰላምና ለሕግ የበላይነት መስፈን መታገል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!