
ጎንደር: ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በጎንደር ከተማ ተገኝተው ከነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ ጎንደር ሰላሟ ተጠብቆ የተጀመሩ ልማቶች ሁሉ ከዳር ደርሰው ሕዝብን እንዲያገለግሉ ነዋሪዎች ንቁ ተሳታፊ መኾን አለባቸው ብለዋል።
በጎንደር ከተማ የጸጥታ ችግር ታሪክ እንዲኾን እና ለልማት ምቹ የኾነ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ነዋሪዎች የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸውም አሳስበዋል። በስኁት አካሄድ ሰላምን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ አካላት ሲያጋጥሙ አባቶች እና እናቶች መምከር እና መገሰጽ፤ የሃይማኖት አባቶችም በየቤተ እምነቶቻቸው ስለሀገር እና ሕዝብ ሰላም በማስተማር ኀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
የሁላችንም መኩሪያ የሚኾኑ ታሪክ እና እሴቶችን ለያዘችው ጎንደር ሰላም እና ልማቷን ጠብቀን ልንይዝላት ይገባል:: የከተማዋን ታሪክ እና የሕዝቡን ኑሮ ወደ ኃላ ለሚጎትቱ ነገሮችም ጆሮ መንሳት ያስፈልጋል ሲሉም አስገንዝበዋል። ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ “ሰላም በመንግሥት ብቻ ተባርካ የምትቀርብ መና አይደለችም፤ ይልቁንም ሕዝቡም ጭምር በጋራ ቆሞ የሚጠብቃት የጋራ ሃብት ናት” በማለት የሰላምን የወል ሃብትነት በአንክሮ ተናግረዋል።
መንግሥት በጎንደር ከተማ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ የነዋሪዎችን ጥያቄ ለመመለስ ይሠራል ሲሉም ርእሰ መሥተዳድሩ አረጋግጠዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ርእሰ መሥተዳድሩ ተገኝተው ነዋሪዎችን በማወያየታቸው ምስጋና አቅርበዋል። ተሳታፊዎች በርካታ ሃሳቦችን ያነሱ ሲኾን ዋና ዋናዎቹ ከዚህ በታች ቀርበዋል:-
👉 ጎንደር ባላት ጸጋ ልክ እንድትለማ የክልሉ መንግሥት ከዚህም በላይ ትኩረት መስጠት አለበት
👉የፋሲል አብያተ መንግሥት የእድሳት ሥራ አስደስቶናል፤ በወቅቱ እንዲጠናቀቅ በትኩረት ይሠራ፣
👉 የትውልድ ክፍተት ለመፍጠር በሚመስል አካሄድ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ታግደውብናል፤ በአስቸኳይ ትምህርት ቤት እንዲከፈት መንግሥት ጥረት ያድርግ፣ ሕዝቡም የበኩሉን ቁርጠኛ አቋም ይያዝ፣
👉 ጎንደር የሰላም እና የቱሪዝም ከተማ ናት፤ ሰላሟን የሚያውኩ ሁሉ እጃቸውን ይሰብስቡ፣
👉 ጎንደር የእምነት እና የሃይማኖት ከተማ እንጅ የሽፍታ ሀገር እንድትባል አንፈልግምና ወደ ጫካ የገቡ አካላት ወደ የቤታቸው ይመለሱ፣
👉 የከተማዋ የኮሪደር ልማት በፍጥነት እየተሠራ መኾኑ አስደስቶናል፣ በየመንገዱ የሚነሱ ኮንቴነሮች ግን በአስቸኳይ ትክ ቦታ ያግኙ
👉 ጎንደር የፋሲል እና የቴዎድሮስ መገኛ ናት፣ ይህንን ታሪክ በሚመጥን መልኩ የቅርስ ጥገና እየተደረገላት መኾኑ አስደስቶናል።
👉ጎንደር የሃይማኖት ሀገር ናት፤ የሃይማኖት አባቶች አጥፊዎችን በማስተማር ወደ ሰላም ይመልሱ በማለት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳድር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በጎንደር ከተማ እና በአካባቢው የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ የክልሉ መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ ነው ብለዋል። የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች የነዋሪዎችን ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል።
በተለይም በኮሪደር ልማቱ ምክንያት የሚነሱ ኮንቴይነሮችን ሁነኛ የገበያ ቦታ ገንብተው እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል። “የሰላማችን ጉዳይ ከጎንደር አባቶች እና እናቶች ጥበብ በላይ አይኾንም” ያሉት ከንቲባው አጥፊን በመምከር ሰላምን ማስፈን ከሁሉም ነዋሪዎች ይጠበቃል ብለዋል። ለዚህም መመካከር እና መደማመጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!