
ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ሕዝባዊ የሠላም ውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የክልል ከፍተኛ መሪዎች፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መሪዎች እና የወረዳው የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የእንሳሮ ወረዳ ነዋሪዎች ለሰላም መስፈን የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸው፤ በአካባቢያቸው ያለው የልማት እንቅስቃሴ እንዲጠናከርም ጠይቀዋል።
በምክትል ርእሠ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) በእንሳሮ ወረዳ ለሚ ከተማ እና አካባቢው ያለው ልማት ለሌሎች አካባቢዎች በምሳሌነት የሚታይ ነው ብለዋል።
ሰላም የኹሉም መሠረት ነው ያሉት ዶክተር አሕመዲን የአካባቢው ማኅበረሠብ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት እንዳሳየ ገልጸው ይህንንም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ መንግሥት ለሰላም መስፈን አበክሮ እየሠራ ነውም ብለዋል። አኹን ያለውን የክልሉ አንፃራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እየተሠራ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ አለማየሁ በበኩላቸው የአካባቢው ማኅበረሰብ ለሰላም ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል። ሕዝቡ ለሚያነሳቸው የመልማት ጥያቄዎችም ዞኑ ጠንክሮ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የኮማንዶ እና አየር ወለድ አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ ሰላማዊ ንግግርን መለማመድ መልካም ስለመኾኑ ገልጸዋል። ከሰላም በተቃራኒ የቆሙ ነገሮች ኹሉ ውጤታቸው ጥፍት ስለመኾኑም አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!