
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ባንክ ጋር ባደረገው ስምምነት የራሱን ስትራቴጂ ቀርጾ ሥራ ጀምሯል፡፡ የፕሮጀክቱ ሁለተኛ ምዕራፍ በክልሉ 18 ከተሞችን ያካተተ መኾኑ ተገልጿል፡፡ በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ከኾኑት መካከል ወይዘሮ ረህመት አድነው አንዷ ናቸው፡፡ የሁለት ልጆች እናት የኾኑት ወይዘሮ ረህመት በጎንደር ከተማ ቅዳሜ ገበያ የቀበሌ 09 ነዋሪ ናቸው፡፡ ከሱዳን ካርቱም ተፈናቅለው እንደተመለሱ ይናገራሉ፡፡
“የነበረኝን ጥሪት ቤት ተከራይቼና ልጆቼን ይዤ ለመኖር እየተዘጋጀሁ ሳለ ሙሉ ንብረቴን ሌቦች ሰረቁኝና ባዶ እጄን ቀረሁ፤ አማራጭ ስላልነበረኝ ለሁለት ዓመት ልጆችን ለማሳደግ እና ኑሮን ለማሸነፍ በየሰው ቤት የቀን ሥራ በመሥራት እተዳደር ነበር” ብለዋል። በ2014 ሕዳር ወር ላይ በከተማዋ ያሉ በኑሯቸዉ አቅመ ደካማ ለኾኑ ዜጎች የሴፍቲኔት ፕሮግራም ጥሩ እድል ይዞ በመምጣቱ ወይዘሮ ረህመትም የእድሉ ተጠቃሚ ኾኑ። በሦስት ቤተሰብ 1 ሺህ 800 ብር በወር እየተከፈላቸው ከሚያገኙት ደግሞ 288 ብር እየቆጠቡ ሥራውን እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡
በወር ከሚከፍላቸው ክፍያ በተጨማሪ ስለ ቁጠባ ፣ ሌሎችንም የክህሎት ሥልጠናዎች ይሰጠን ነበርም ነው ያሉት፡፡ ሥልጠናው አመለካከታቸውን በደንብ እንደቀየረው የሚናገሩት ወይዘሮዋ የሴፍቴኔት ፕሮግራሙ አንድን ቤተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርገው ለሦስት ዓመታት በመኾኑ ከፕሮጀክቱ ተመርቄ እንደወጣሁ በ26 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ሱቅ በመክፈት ሽሮና በርበሬ እያዘጋጀሁ ለሚፈልጉ የአካባቢው ነዋሪዎች በማከፋፈል ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ጠንክረው በመሥራት የነበራቸውን ካፒታል ወደ 400 ሺህ ብር በማሳደግ የተሻለ ኑሮ እንደሚኖሩና ለልጆቻቸው አስፈላጊ ግብዓቶችን ማሟላት ችያለሁ ነው ያሉት። ከራሳቸው አልፈውም አምስት ጓደኞቻቸውን በማስጠጋት ምጥን እያዘጋጁ በማከፋፈል ሥራ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በክልሉ በርካቶችን ተጠቃሚ እያደረገ የሚገኘው የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በ2009 ዓ.ም በደሴ ከተማ እንደተጀመረ የአማራ ክልል የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ ሐሰን ኑሩዬ ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱን መጀመር ያስፈለገበት ምክንያት የከተሞች በየጊዜው በፍጥነት ማደግ፤ በከተማ ውስጥ ያለው የድህነት መጠን እየተባባሰ መምጣት እና ከገጠር እየፈለሰ ወደ ከተማ የሚመጣው ሰው መብዛት የከተማ ድህነትን የከፋ እንዳደረገው ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው ይላሉ፡፡ ፕሮጀክቱ በፌዴራል ደረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ባንክ ጋር ባደረገው ስምምነት የራሱን ስትራቴጂ ቀርጾ እንደተጀመረ አስተባባሪው ጠቁመዋል።
ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2013 ዓ.ም በደሴ ከተማ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገው ፕሮጀክት ሥራውን በማስፋት ከ2014 እስከ 2018 ዓ.ም የሚቆይ ሁለተኛ ምዕራፍ በክልሉ በ18 ከተሞች እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ዜጎች ሠርተው ክፍያ እንዲከፈላቸው ማድረግ፣ በሥራቸው የከተሞችን ገጽታ እንዲቀይሩ ማድረግ እና የሥራ ባሕልን በማሳደግ ሠርተው ከድህነት እንዲወጡ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር በዋናነት ዓላማ አድርገን እየሠራን ነው ብለዋል።
በሥራው ተሳታፊ ለኾኑ ዜጎች የተረጅነትን አመለካከት እና አስተሳሰብ ለመቀየር የክህሎት፣ የቴክኒክ እና የቁጠባ ባሕልን እንዲያሳድጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና እንደሚሰጥም ገልጸዋል። እስካሁን ምንም ዓይነት ገንዘብ ያልነበራቸው የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች ከ500 እስከ 600 ሺህ ብር ድረስ በአይነትም በጥሬ ገንዘብም ጥሪት በማፍራት ውጤታማ መኾናቸውን ነው የተናገሩት አስተባባሪው፡፡
በዚህም የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች በኑሯቸው ላይ መሰረታዊ ለውጥ የታየ መኾኑ እንደ ሀገር ጥሩ ተሞክሮ ነውም ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ለተጠቃሚዎች አጠናክሮ በማስቀጠል ከድህነት መላቀቅ እንችላለን የሚለውን አስተሳሰብ በመገንባት በሦስት ዓመት ውስጥ “ጥሪት ለዘላቂ ህይወት” በሚል መሪ ሀሳብ በንቅናቄ ሥራ እንደተከናወነ ነው የገለጹት፡፡
እስካሁን ባለው በክልሉ ከ100 ሺህ ዜጎች በላይ በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ ፕሮግራም በተመረጡ ከተሞችና በፕሮጀክቱ ለሚታገዙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ብቻ መኾን የለበትም ነው ያሉት አስተባባሪው።
የውጭ ሀገር እርዳታን ሳንጠብቅ የከተማው መሪዎች፣ ማኅበረሰቡና ባለሀብቶች በሁሉም ከተሞች ያሉ ተፈጥሯዊ ጸጋዎችን በመለየትና ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት በከተማ ውስጥ ያሉ ዝቅተኛ ነዋሪዎችን እና ሥራ አጥ ዜጎችን ወደ ሥራ በማስገባት ይገባል ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!