ለሦስት ወራት የሚቆይ የኪነ ጥበብ ዘመቻ በመላው ሀገሪቱ እንደሚደረግ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

42

አዲስ አበባ: ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከክልል እና ከከተማ አሥተዳደር መሪዎች ጋር በፖሊሲ እና ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር በማድረግ ላይ ነው። በምክክር መድረኩ ላይም የሩብ ዓመቱ የሥራ አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በመድረኩ ለቀጣይ ሦስት ወራት በሚቆየው የኪነ ጥበብ ዘመቻ ላይ ስለሚከወኑ ኩነቶች ዝርዝር ማብራሪያ ተነስቷል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ኢትዮጵያ በባሕል እና ስፖርት ዘርፍ እምቅ ሃብት ያላት በመኾኑ ያላትን ፀጋ በተገቢው መንገድ በመጠቀም የዓለም ትኩረት ለመሳብ በትጋት መሥራት ይጠበቅባታል ብለዋል፡፡ ሰላምን ለሕዝቡ ለመስበክ የኪነ ጥበብ ዘርፉን መጠቀም የተሻለ መኾኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ ኪነ ጥበብን እና ባሕላዊ እሴቶችን ለሀገር ገጽታ እና ለትውልድ ግንባታ መጠቀም ይገባል ብለዋል።

ሚኒስትሯ ከቀጣይ ኅዳር 7- 2017 ዓ.ም እስከ የካቲት 7-2017 ዓ.ም የሚቆይ የኪነጥበብ ንቅናቄ በመላ ሀገሪቱ እንደሚጀመርም ነው ያብራሩት፡፡ በኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በመታገዝ ግጭቶችን ለመፍታት እና ሰላምን ለማስፈን ለሦስት ወር ንቅናቄውን በማድረግ ለሕዝቡ በኪነ ጥበብ የተደገፈ ሥራ ይሠራልም ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
Next article“ከ100 ሺህ ዜጎች በላይ በከተማ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ተጠቃሚ ኾነዋል” የአማራ ክልል ከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት